ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በተካሄደው 7ኛ ሀገራዊ ምርጫ ይፋ ከተደረጉት 501 መቀመጫዎች ውስጥ 438ቱን ያገኘው የብልጽግና ፓርቲ አዲስ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን ድምፅ አግኝቶ ማሸነፉ ታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቀጣይ ዓመት መስከረም በሥልጣናቸው ለመቀጠል ቃለ መሃላ ይፈጽማሉ። ይህ ለዶ/ር ዐቢይ ደጋፊዎች ትልቅ ድል በመሆኑ በበላይነት የመሩትን የኢኮኖሚ ለውጥ እንደሚያስቀጥሉ ያምናሉ።
ምንም እንኳን ምርጫው በተለይ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች የግጭት ጥላ ቢያጠላበትም፣ የጭቆና ክሶች ቢሰሙም እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ተሳትፎ አናሳ ቢሆንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ፓርቲ በአገሪቱ አጠቃላይ ምርጫ ከፍተኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ በማሸነፍ የበላይቱን ይዞ ለመቀጠል ችሏል።
የ49 ዓመቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሥልጣን የመጡት በአውሮፓውያኑ 2018 የተካሄዱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ ሲሆን፣ መጀመሪያ ላይ ስለአንድነት ባደረጉት ጥሪ ከፍተኛ ተቀባይነትን ቢያገኙም፤ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የአገሪቱን መንግሥትን ተቆጣጥረው ከቆዩት ከትግራይ ፖለቲከኞች ጋር ተቃቅረዋል።
ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ከአንድ ዓመት በኋላ በዋናነት ከኢትዮጵያ ሰሜናዊ ጎረቤት ከኤርትራ ጋር የነበረውን አስርታት ያስቆጠረ ፍጥጫን ለማስቀረት በወሰዱት እርምጃ ምክንያት የኖቤል የሰላም ሽልማትን አሸንፈዋል።
በአገሪቱ የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች የሚካሄዱት ኃይለኛ የታጣቂዎች እንቅስቃሴ ስለማብቃታቸው ምልክቶች ባለማሳየታቸው የደኅንነት ባለሙያዎች አገሪቱ ወደ ጦርነት ልትመለስ እንደምትችል ይሰጋሉ።
በምርጫው ቀን፣ ከመንግሥት ኃይሎች ጋር የሚዋጉት ታጣቂ ቡድኖች በፈጠሩት የደኅንነት ስጋት ምክንያት በአገሪቱ በርካታ ሕዝብ በሚኖርባቸው ሁለቱ ክልሎች ውስጥ 143 የምርጫ ጣቢያዎች ሳይከፈቱ ቀርተዋል።
በአማራ ክልል የፋኖ ሚሊሻዎች እና በበሽብር ቡድንነት የተፈረጀው በኦሮሚያ ክልል የሚንቀሰቀሰው የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሁለቱም ምርጫውን እና ውጤቱን ውድቅ አድርገዋል።
ኦነግ በኦሮሚያ ክልል እጩዎች አቅርቦ የተወዳደ ቢሆንም አንድ ቦታም ሳያሸንፍ መቅረቱ ታውቋል፡፡ ለኦሮሚያ ምክር ቤት የተወዳደረው ኦነግ አንድም ወንበር ሳያገኝ ኢዜማ በኦሮሚያ ምክር ቤት አንድ መቀመጫ ማሸነፉ ተገልጿል።
በምርጫው ከተሳተፉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከፍተኛውን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ያገኘው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሲሆን 13 መቀመጫዎችን አሸንፏል።
ስምንት የግል ዕጩዎች፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) 6፣ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) 3፣ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ኃይል ንቅናቄ 3፣ ነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ 3፣ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ 2 መቀመጫዎችን ሲያሸንፉ አምስት ፓርቲዎች ደግሞ አንድ አንድ መቀመጫ አግኝተዋል።
በተጨማሪም ብልጽግና ምርጫ በተካሄደባቸው 11 የአገሪቱ ክልሎች ውስጥ እንዲሁም በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ እና በድሬ ዳዋ ምክር ቤቶች ውስጥ ካሉት መቀመጫዎች አብዛኛውን አግኝቷል። ብልጽግና በፌደራል፣ በክልል እና በከተሞች መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለውን የምክር ቤት መቀመጫዎችን አሸንፏል።
በዚህም የኦሮሚያን 523፣ የአማራ 257፣ የሶማሌ 214፣ የሲዳማ 175፣ የጋምቤላ 176፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ 143፣ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 144፣ የደቡብ ኢትዮጵያ 182፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ 145፣ የአፋር 124፣ የሐረሪ 32፣ የአዲስ አበባ 134 እና የድሬዳዋ 161 የምክር ቤት መቀመጫዎችን ዕጩዎቹ አሸንፈዋል።














