Image

ከወራት በፊት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ የገባችበትን ውዝግብ ለመፍታት ዳግም ለማደራደር ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸው ይታወቃል።

በወቅቱ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ሲናገሩ እሳቸው በግላቸው ከግብፁ መሪ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ጋር ባላቸው የወዳጅነት መንፈስ እና አሜሪካ ለግብፅ ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ባላት ቁርጠኝነት፣ በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ‘የአባይን ውሃ መጋራት’ ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በኃላፊነት መንፈስ ለመፍታት አደራዳሪነቷን ዳግም ለመጀመር ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር፡፡

በዚህ ሳምንት ከጁን 15 እስከ 17 ቀን 2026 ዓ.ም በፈረንሳይ አዘጋጅነት በተካሄደው የጂ 7 ሀገራት ስብሰባ ላይ ከአፍሪካ ተጋብዘው ስብሰባውን የተካፈሉት የግብጹ ፕሬዝዳንት አልሲሲ ከአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ተገናኝተው በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ውይይት አካሂደዋል፡፡

በውይይታቸውም የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር የገባችውን አለመግባባት “ቅድሚያ ሰጥተው” እንደሚመለከቱት እና ፍትሐዊ የሆነ መፍትሄ እንደሚፈልጉለት ተናግረዋል።

አሜሪካን ጨምሮ ፈረንሳይ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ጃፓን፣ ጣልያን እና ካናዳ አባል በሆኑበት እንዲሁም የአውሮፓ ኅብረት በተካተተበት የበለጸጉ አገራት ስብስብ በሆነው የቡድን ሰባት ጉባዔ ላይ ከአፍሪካ የግብፅ እና የኬንያው መሪ ተሳትፈዋል።

በዚህ ጉባዔ አጋጣሚ ትራምፕ ከአል ሲሲ ጋር በጋዜጠኞች ፊት ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ የተገነባው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ “በግብፅ ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሆነ አውቃለሁ” ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከሱዳን እና ግብፅ ጋር አለመግባበት ውስጥ ቆይታለች።

ግብፅ ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለአስራ አራት ዓመታት በአባይ ወንዝ ጉዳይ ላይ ከስምምነት ለመድረስ ሲደራደሩ የነበረ ቢሆንም ሦስቱንም አገራት የሚያስማማ ሁሉን አቀፍ መግባባት ላይ መድረስ አልተቻለም።

ኢትዮጵያ በ2017 ዓ.ም መጨረሻ ላይ አጠናቅቃ ያስመረቀችው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ከ5000 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌትሪክ ኃይል ያመነጫል። ትራምፕ በተለያዩ ጊዜያት ስለ ሕዳሴ ግድብ ከኢትዮጵያ ተቃራኒ የሆነ አቋም ሲያራምዱ እና ለግብፅ ወግነው አስተያየት ሲሰጡ ተደምጠዋል።

በጥር ወር ፕሬዝዳንቱ ለግብፁ አቻቸው አብደል ፈታህ አል ሲሲ በጻፉት ደብዳቤ የሕዳሴ ግድብን የተመለከተ ድርድር ለመጀመር እንደሚፈልጉ ገልጸው ነበር። ፕሬዝዳንት ትራምፕ በዚህ ደብዳቤያቸው ላይ “በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን ‘የአባይን ውሃ መጋራት’ ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በኃላፊነት መንፈስ ለመፍታት ዝግጁ ነኝ” ብለው ነበር።

ኢትዮጵያ በዚህ ለግብፅ በቀጥታ በተጻፈ ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰችው በግልባጭ እንዲደርሳት ብቻ ነው። የግብፁ ፕሬዝዳንት አልሲሲ እና የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በፈረንሳይ ተገናኝተው ሲወያዩ ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ነው።

ፕሬዝዳንት አልሲሲ የአባይ ወንዝ ጉዳይ ለግብፅ ያለውን ጠቃሚነት ተናግረው ትራምፕ ጉዳዩን ለመፍታት ፍላጎት በማሳየታቸው አመስግነዋል።

“ከግብፅ ፕሬዝዳንት ጋር በመገናኘቴ ክብር ይሰማኛል” ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት “እሱ በመላው ዓለም የተከበረ ሰው ነው። ግንኙነታችን ጠንካራ ነው። የግል ግንኙታችንም ለረዥም ጊዜ እንዲሁ ጠንካራ ነው” ሲሉ አል ሲሲን አሞካሽተዋል።

ትራምፕ አክለውም “በግድቡ ፕሮጀክት ጉዳይ እያገዝኩት ነው፤ በጋራ እየሠራንበት ነው” በማለት በጥምረት እየሠሩ መሆኑን አረጋግጠዋል። “ኢትዮጵያ ፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ ነው ግብፅን እና የግድቡን ጉዳይ እያስተናገደች ነው ያለችው” ያሉት ትራምፕ፣ ከግብፅ ጋር ከአባይ ባሻገር በንግድ ጉዳዮችም አብረው እንደሚሠሩ ጠቅሰዋል።

“የናይል ውሃ መሆን ከነበረበት መጠኑ ዝቅ እያለ ነው ያለው። . . .በኢትዮጵያ ግድብ ተገንብቷል። ብዙ ችግር በግብፅ ላይ እያደረሰ እንደሆነ አውቂያለሁ” ብለዋል። የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው የግድቡን ጉዳይ ፈትተውት እንደነበር ጠቅሰው ነገር ግን “በተጭበረበረ ምርጫ” ተሸንፈው ነገሮች መበላሸታቸውን ተናግረዋል።

በመቀጠልም “እስኪ በድጋሚ ነገሩን እናየውና ችግሩን እንፈታዋለን” ሲሉ ለአል ሲሲ ቃል ገብተዋል። በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን በአሜሪካ እና በዓለም ባንክ አሸማጋይነት ተከታታይ ድርድሮች በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል መደረጋቸው ይታወሳል።

ነገር ግን ከስምምነት ተደርሶ ይፈረማል በተባለበት በመጨረሻው ሰዓት ኢትዮጵያ የቀረበው ስምምነት ጥቅሟን የሚጎዳ መሆኑን በመግለጽ ባለመፈረሟ ጉዳዩ በእንጥልጥል ቀርቷል። በዚህም ምክንያት የተቆጡት ፕሬዝዳንት ትራምፕ በወቅቱ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ትሰጥ ከነበረው ድጋፍ የተወሰነው እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።

በፈረንሳዩ ውይይት ወቅት የግብፁ ፕሬዝዳንት ለትራምፕ ትልቅ ክብር እንዳላቸው እና በመካከለኛው ምሥራቅ ሰላም አምጥተዋል በሚል ምስጋና አቅርበዋል። “ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለእርስዎ ያለኝን ክብር እና አድናቆት ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። ይሄ ግድብ በግብፅ ላይ እየፈጠረ ያለውን እክል ስለመረዳትዎ ታላቅ አክብሮት አለኝ” ብለዋል፡፡

ግብፅ እና ሱዳን በተደጋጋሚ በአባይ ወንዝ ላይ ኢትዮጵያ የገነባችው ታላቁ ሕዳሴ ግድብ በምሥራቅ የናይል ተፋሰስ አገራት ላይ ዘላቂ ስጋት ደቅኗል ሲሉ ይከስሳሉ። ኢትዮጵያ በግድቡ ምክንያት በተፋሰሱ አገራት ላይ የሚደርስ ጉዳት እንደሌለ በመግለጽ በተፈጥሮ ሀብቷ በፍትሐዊነት የመጠቀም ሕጋዊ መብቷን እንደምትጠቀም በተደጋጋሚ ስትገልጽ ቆይታለች።

ግብፅ ግን በግድቡ የውሃ ይዘት እና የሚለቀቅበት ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ሕጋዊ ስምምነት እንድትፈርም ትፈልጋለች። የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዳግም ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ አገራቸው የግድቡን ግንባታ በገንዘብ ደግፋለች ብለው የተናገሩ ቢሆንም ኢትዮጵያ ግን ከዜጎቿ ውጪ የማንም ገንዘብ በግድቡ ላይ አልዋለም ስትል አስተባብላለች።

እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ፕሬዝዳንት የአባይ ወንዝ ከግብፅ የሚነሳ አድርገው ያስቡ እንደነበር የገለጹበትን ጨምሮ ግድቡ ግብፅን የሚጎዳ መሆኑን በመጥቀስ የግብፅን አቋም የሚደግፍ ተደጋጋሚ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።

ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ተደርጎበት ግንባታው የተካሄደው የሕዳሴ ግድብ 1.78 ኪሎ ሜትር የተዘረጋ ሲሆን 145 ሜትር ከፍታ አለው። በዓለማችን በርዝመቱ የሚታወቀው የዓባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ነው።

የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ በኢትዮጵያ ግድብ መገንባቱ የውሃ መጠን ይቀንስብኛል ስትል በተደጋጋሚ ብትከስስም ኢትዮጵያ ግን ውንጀላውን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።

ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና አብዛኛውን የወንዙን ውሃ ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት በመጥቀስ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት አላት በማለት ኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳላበት ስትከራከር ቆይታለች። ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ታላቁ የሕዳሴ ግድብ የግብፅ የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ የሚጥል አይደለም ስትል በተደጋጋሚ ገልጻለች።

እንግሊዝ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስጠነቀቀች

እንግሊዝ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስጠነቀቀች

ሻዕቢያን ከሳህል በረሃ የትጥቅ ትግል ዘመን ጀምሮ ኤርትራን ገንጥሎ መንግስት እስከሚሆን ድረስ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት አጋር ሆነው የፋይናስና…

ጥቅም 15, 2026
ኦነግ ለኢሳይያስ ንግግር በመግለጫ ምላሽ ሰጠ

ኦነግ ለኢሳይያስ ንግግር በመግለጫ ምላሽ ሰጠ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትናንት ባወጣው መግለጫ “ህዝባችን ላይ የታወጀና በቀጣናው ደግሞ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እየጠነከሩ በመምጣታቸው እንዲሁም…

ጥቅም 14, 2026
የተቋረጠው የትግራይ በረራ በድጋሚ መጀመሩ ምን ያመለክታል?

የተቋረጠው የትግራይ በረራ በድጋሚ መጀመሩ ምን ያመለክታል?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜያዊነት ተቋርጦ የነበረውን ወደ መቀሌ ከተማ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ እሁድ ከጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ…

ጥቅም 12, 2026
ኢትዮጵያ ስለተፈጸመባት ወረራ ለተመድ የፀጥታ ም/ቤት አሳወቀች

ኢትዮጵያ ስለተፈጸመባት ወረራ ለተመድ የፀጥታ ም/ቤት አሳወቀች

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት…

ጥቅም 12, 2026