ያለፌዴራል መንግስት እውቅና በትግራይ ክልል መንግስታዊ መዋቅሩን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ሕወሓት፣ የመንግስት ባለስልጣናት በትግራይ ላይ የድሮን ጥቃቶችን እየፈጸሙ፣ የወታደራዊ ዘመቻ ዝግጅት እያደረጉ እና ወደ ክልሉ የሚገባ ነገር እንዳይኖር እየሰሩ ነው ብሏል፡፡ የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት በፊናቸው ሕወሓትን በጦርነት እንቅስቃሴ ይከሳሉ፡፡
ከፕሪቶሪያው ስምምነት ውጭ ያለፌዴራል መንግስት እውቅና በትግራይ ክልል መንግስታዊ መዋቅሩን ተቆጣጥሮ የሚገኘው ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ተግራይ (ህወሓት) የፌዴራል መንግስትን በሌላ የአውዳሚ ጦርነት ዝግጅት እየከሰሰው ይገኛል፡፡
ሕወሓት በፌዴራል መንግስት ላይ ባቀረበው በዚህ ክስ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ባለስልጣናት በትግራይ ላይ የድሮን ጥቃቶችን እየፈጸሙ፣ የወታደራዊ ዘመቻ ዝግጅት እያደረጉ እና ወደ ክልሉ የሚገባ ነገር እንዳይኖር እየሰሩ ነው ብሏል፡፡
የፌዴራል መንግስት ባለስልጣናት በፊናቸው ሕወሓትን በጦርነት እንቅስቃሴ ይከሳሉ፡፡ በክልሉ ያለውን ፖለቲካዊ ሁናቴን በቅርበት የሚከታተሉ ተንታኞች እንደሚሉት ግን፤ ጦርነቱ እንዳይካሄድ ሁነኛ ውይይት ማድርግ ያስፈልጋል፡፡
ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ከሁለት ቀናት በፊት ሰኞ ባወጣው ይፋዊ መግለጫ በብልጽግና ፓርቲ የሚመራው የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት “አሁንም የጦርነት ከበሮ እየመታ ይገኛል” በማለት ለሌላኛው ዙር ደምአፋሳሽ ጦርነት ዝግጅት በማድረግ ከስሷል፡፡
እንደ ሕወሓት መግለጫ፤ የፌዴራል መንግስት በትግራይ በተለያዩ አከባቢዎች የድሮን ጥቃት እየፈጸመም ይገኛል፡፡ በኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ሕገወጥ ተደርጎ የሚታይና በምርጫ ቦርድ እውቅና የተነፈገው ፓርቲው የፌዴራሉ መንግስትን በሺዎች የተፈናቀሉትን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ወደ ቀየያቸው ከመመለስ ይልቅ ወደ ትግራይ መድሃኒትን ጨምሮ መሰረታዊ እቃዎች እና አገልግሎቶች እንዳይገቡ ከበባ በማድረግ ላይ ይገኛልም ሲል ወቅሷል፡፡
ከወልቃይትና ሁመራ አከባቢዎች በጦርነት ምክንያት ጉዳት ደርሶባቸው ለተፈናቀሉ የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ላለፉት ሶስት ወራት የተደረገላቸው ድጋፍ ባለመኖሩ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ወድቀዋልም ነው ያለው፤ ሕወሓት በሰሞነኛው መግለጫው፡፡
የፌዴራል መንግስት በፊናው ሕወሓትን በተደጋጋሚ የጦርነት እንቅስቃሴ በማድረግና የፌዴራሉ መንግስት ላይ ጦርነት ለመክፈት ዝግጅት ላይ በመሆን ይከሰዋል፡፡ በቅርቡ እንኳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች አማካሪ አቶ ጌታቸው ረዳ እና የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሬድዋን ሁሴን በአልጄዚራ ያጋሩት ጽሁፍ ለዚህ ማሳያ ነው፡፡
በጽሁፉ ላይ ባለስልጣናቱ እንዳመለከቱት “የህወሓት ፅንፈኛ ቡድን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት በመጣስ ከኤርትራ ጋር በማበር በአጭር ቀናት ውስጥ ጥቃት ሊሰነዝር ዝግጅት እያደረገ ነው” ሲሉ ክስ አቅርበዋል።
በትግራይ ክልል አሁን ላይ እየተስተዋለ ላለው የፖለቲካ ትኩሳት በሁሉም አቅጣጫ ወደ መፍትሄ እየወሰደ ያለውን ነገር እየተመለከትን አይደለም ሲሉ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የክልሉን ፖለቲካዊ ሁናቴ በቅርበት የሚከታተሉት ፖለቲከኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ አቶ መስፍን ደሳለኝ፤ ይመለከተኛል የሚለው ገለልተኛ አካል በመሃል ገብቶ ካላደራደረ የሌላኛው ዙር ደም አፋሳሽ ጦርነቱ መከሰት አይቀረ ይመስላል ብለዋል፡፡
ፖለቲከኛው፤ “ይመለከተኛል የሚለው ዓለም ዓቀፍ ገለልተኛ አካል ማደራደር ካልቻለ ወደ ጦርነት የሚገቡበት እድሉ በሰፊው ይታየኛልም” ብለዋል፡፡
አቶ መስፍን እንደሚሉት ምንም እንኳ መጠኑ ሊበላለጥ ቢችልም፤ ችግሮች ከሁለቱም አቅጣጫ ይስተዋላሉ፡፡ ሆኖም አንዱ ሌላውን ተወቃሽ እና ተከሳሽ ከማድረግ ይልቅ ለድርድር የሚበጅን ቀዳዳ በመፈለግ ግጭቱን ማስቀረት የሚያስችል መንገድ ላይ መጠመድ ለሁሉም የሚበጅ እንደሚሆንም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
“በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የተለመደ መጥፎ ባህል የራስን ጥፋት ሳይመለከቱ ጩኸት መቀማት ነው” ሲሉም የገለጹት ፖለቲከኛ እና ፖለቲካ ተንታኙ፤ የህዝቡን ችግር በዘላቂነት ሊፈታው በሚችለው ፖለቲካዊ እርምጃ እና የፖለቲካ መፍትሄ ላይ በመጠመድ በዚያም በዚህም የሚታይ ያሉትን ግጭት ማስቀረት እንደሚቻልም እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግስት ‘የጥፋት ኃይሎች’ ካላቸው አካላት ባዕዳን ካላቸው የውጭ ጠላት ጋር በማበር “ፅምዶ የሚል ቁርኝት በመፍጠር ዕኩይ የጥፋት ዝግጅት ፈጽመዋል” ሲል ተከሳሽ ከሚደርጋቸው የታጠቁ አካላት አንዱ ሕወሓትን ነው፡፡ በቅርቡ እንኳ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት ባወጣው ይፋዊ መግለጫ ምርጫውን በማደናቀፍ በመጣር እነዚህን “ፅምዶ” ብሎ የጠራቸውን አካላት ከሷል።
የጠላት ኃይሎች በመደጋገፍ በተወሰኑ አካባቢዎች ዒላማ አድርገው ነጥሎ ለማጥቃት ተንቀሳቅሰዋል ያሏቸው እነዚህ አካላት የጦር መሣሪያ፣ ተተኳሾችንና ሌሎች ሎጀስቲክሶችን በድጋፍ በማቅረብ በደቡባዊ ትግራይ በሚገኙ አዋሳኝ የአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ላይ ትንኮሳ ፈጽመዋል ሲል በማሳያነት ማቅረቡ የሚታወስ ነው፡፡
ሕወሓት በሰሞነኛው መግለጫ እንዳብራራው ግን “የፌዴራል መንግስት በቅርቡ ባወጣው መግለጫ የትግራይ ኃይሎችን በጦርነት ናፋቂነት መክሰሱ ለራሱ የሚያደርገው የጦርነት ዝግጅት ግልባጭ ነው” ሲል ሞግቶ ይተቻል፡፡
በዚህም መንግስትን ጉዳዩ የሚያሳስባቸው የአገር ውስጥ ዜጎች እና የዓለማቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት ነው ሲል ወቅሷል፡፡ ልዩነቶችን በሰላማዊ ንግግር እና ውይይት የመፍታት መንገድን እንደሚደግፍም የጠቆመው ሕወሓት፤ በሌላ በኩል እራስን ለመከላከል ላለው ዓለማ ማህበረሰቡ እንዲዘጋጅ ጥሪ አቅርቧል፡፡
የፖለቲካ ተንታኙ አቶ መስፍን ደሳለኝ እንደሚሉት ግን፤ አሁን ላይ ለጦርነት የመዘጋጀት ዓለማ ያለው ማህበረሰብ ማየት ከባድ ነው ይላሉ፡፡ “የተደራጀው የፖለቲካ ኃይል ነው የሚወስነው እንጂ ማህበረሰቡ በምንም መልኩ ጦርነት ውስጥ የመግባት ምንም አይነት ፍላጎት የለውም” ነው ያሉት፡፡
አሁን በተያዘው መንገድ የትግራይም ሆነ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ችግር መፍታት አይቻልም በማለትም አንዳች የተለየ የፖለቲካ አካሄድ በመከተል አሊያም የዓለማቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ በመግባት ለአስገዳጅ ውይይት በማስቀመጥ መፍትሄ እንዲመጣ እንደሚሹ አስረድተዋል፡፡














