የትግራይ ክልል መሪዎች ለወታደራዊ ግዳጅ ምልመላ ለማድረግ “ኃይል የሚሰጣቸውን” እና ተቃዋሚዎችን እንዲቀጡ “መንገድ የሚጠርግላቸውን” ረቂቅ አዋጅ እንዲሰርዙ ሂውማን ራይትስ ዋች አሳሰበ።
ህወሓት ያወጣውና ከፍተኛ ውዝግብ ያስነሳው አዲሱ ረቂቅ አዋጅ “የሕዝብን ኅልውና እና ደኅንነት ለማረጋገጥ የወጣ አዋጅ” ይሰኛል። ከጦርነቱ በፊት በነበረውና በህወሓት አማካኝነት ዳግም በተቋቋመው የትግራይ ክልል ምክር ቤት የቀረበው ይህ ባለ 44 ገጽ ረቂቅ ሕግ፣ በነዋሪዎች፣ በተቃዋሚዎችና በዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ ከፍተኛ ትችትና ስጋት ፈጥሯል።
የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም ሰኔ 16/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ ህወሓት ረቂቅ አዋጁን ያወጣው በፌደራል መንግሥቱ የተሾሙ የክልሉን አስተዳዳሪዎች ከሥልጣን አውርዶ “ከኤርትራ ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት ጋር የሚመሳሰል አፈሳ ከጀመረ በኋላ ነው” ብሏል።
የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሻ ባድር “የትግራይ ተወላጆች ከሁለት ዓመቱ አውዳሚ ግጭት እና ካስከተለው መዘዝ ገና እያገገሙ” እንደሆነ ጠቅሰው፤ “የክልሉ ባለሥልጣናት አሁን ባለው የፖለቲካ ውጥረት ሳቢያ ሲቪሎች ወታደራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ማስገደድ እና ጎን ለጎን ደግሞ የግዳጅ ምልመላውን የሚተቹትን መቅጣት የለባቸውም” ብለዋል።
“የትግራይ ሕዝብን ኅልውና እና ደኅንነት ለማረጋገጥ የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ያወጣው አዋጅ” በሚል ርዕስ የተዘጋጀው ረቂቅ ሰነድ በክልሉ ምክር ቤት እንደሚጸድቅ ቢቢሲ ትግርኛ ከምንጮቹ ያገኘው መረጃ ይጠቁማል።
በረቂቅ አዋጁ የመጀመሪያ ክፍል አንቀጽ 5 ላይ ዕድሜ እና ጤና የሚፈቅድለት ማንኛውም የትግራይ ተወላጅ የክልሉ መንግሥት የሚያቀርብለትን የክተት ጥሪ ተቀብሎ የመሳተፍ “ብሔራዊ ግዴታ” እንዳለበት ይገልጻል።
በሦስተኛው ክፍል ደግሞ “የወንጀል ተጠያቂነት” በሚለው የረቂቅ ሕጉ ክፍል ሥር፣ በትግራይ ጦር ውስጥ ለመቀላቀል ወይም ለመዋጋት ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው፤ በደጀን ወይም በግንባር ግዴታውን እንዲፈጽም ጥሪ ቀርቦለት ያልተቀበለ ከሆነ፤ ከ10,000 እስከ 50,000 ብር ተቀጥቶ ግዴታውን እንዲፈጽም ይደረጋል ሲል ይደነግጋል።
በትግራይ እየተካሄደ ያለው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ በፈጠረው ስጋት ምክንያት በርካታ ወጣቶች ከክልሉ እየወጡ ወደ ቀሪው የኢትዮጵያ ክፍል እየሸሹ ሲሆን፤ ሌሎች ደግሞ እዚያው ተደብቀው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
አፈሳው ከነዋሪዎች እና ከመብት ተሟጋቾች ውግዘት እየገጠመው ቢሆንም ምልመላው በፈቃደኝነት የሚካሄድ ነው በማለት ህወሓት ማስተባበሉን የፈረንሳይ ዜና ወኪል (ኤኤፍፒ) መዘገቡ ይታወሳል።
በትግራይ በስፋት እየተካሄደ ያለው ወደታራዊ ምልመላ በአብዛኛው “በፈቃደኝነት ላይ ብቻ ተመሥርቶ” የሚካሄድ መሆኑን የህወሓት ምክትል ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል አሰፋ ተናግረዋል።
ነገር ግን ሁሉም የትግራይ ተወላጅ “ግዛቱን ከኅልውና ስጋት መከላከል ስላለበት ልዩ ሁኔታዎች አሉ” በማለት የግዳጅ ምልመላው እንዳለ በተዘዋዋሪ ገልጸዋል።
ሂውማን ራይትስ ዋች ባወጣው መግለጫ፤ ረቂቅ አዋጁ “አሻሚ እና በጣም የተለጠጠ ቋንቋ መያዙን” ይጠቅሳል።
ይህም “ለብዝበዛ ክፍት መሆኑን” እንዲሁም ለተለያዩ ጥፋቶች “እስራት እና የሞት ቅጣትን” ማካተቱን ገልጿል። ረቂቁ የወጣው በህወሓት እና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለው ውጥረት በመባባሱ የትግራይ ንጹኃን ዜጎችን “ለተጨማሪ የጭካኔ ድርጊት” ያጋልጣል የሚል ፍርሃት በተፈጠረበት ወቅት መሆኑን ያመለክታል።
ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች- ኢትዮጵያ የተባለው የሰብአዊ መብት ድርጅት “የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች በክልሉ መጠነ ሰፊ አፈሳ እና የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እያካሄዱ መሆናቸውን” በመጥቀስ መግለጫ ማውጣቱ ይታወሳል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ ወጣቶችም ከሥራ ቦታቸው፣ ከመዝናኛ ሥፍራዎች እንዲሁም ከሕዝብ ትራንስፖርት ላይ በግዳጅ ተወስደው ወደተለያዩ ካምፖች መላካቸውን ተናግረዋል።
ውጥረቱ በተባባሰበት ወቅት፤ አሜሪካ “በኢትዮጵያ ያለውን ሰላም በማናጋት” ውስጥ ተሳታፊ ናቸው ባለቻቸው አክራሪ የህወሓት አባላት እና የቅርብ የቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ ክልከላ መጣሏን ማስታወቋ አይዘነጋም።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ በአክራሪ ህወሓት አባላት እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል በሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት እንዲያገረሽ የሚያደርግ ውጥረት እየተባባሰ መምጣቱን በመግለጽ ይህም “በቀጣናው ያለውን ሰላም እና መረጋጋት የሚያናጋ ነው” ብሏል።
ህወሓት ባወጣው መግለጫ የአሜሪካን የቪዛ ክልከላ “ሚዛናዊ ያልሆነ” ሲል አውግዟል።
የአሜሪካ እርምጃ የትግራይን እውነታ እንደማያንጸባርቅ እና የፌደራል መንግሥቱን “ተጠያቂነት ያላደረገ” መሆኑን በመጥቀስም ኮንኗል።
የህወሓት የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ “ከኤርትራ ብሔራዊ የውትድርና አገልግሎት” ጋር እንደሚመሳሰል እና የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ተቀማትም ይሄንን ማውገዛቸውን ሂውማን ራይትስ ዋች ጠቅሷል።
“የግዳጅ ምልመላ፣ ገደብ የለሽ ወታደራዊ አገልግሎት፣ የእንቅስቃሴ ገደብ እና ከወታደራዊ ምልመላ የሚያመልጡ ሰዎችን እና ቤተሰቦቻቸውን መቅጣትን” የተመድ መርማሪ ተቋማት “በተገቢው ሁኔታ መኮነናቸውን” በመግለጫው አካቷል።
የትግራይ ጦርነትን ያስቆመውን የፕሪቶሪያ ስምምነት ያስተባበሩ ወገኖች፤ ማለትም የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ኬንያ እና ደቡብ አፍሪካ “የትግራይ መሪዎች የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላውን እና ረቂቅ አዋጁን እንዲሰርዙ በይፋ መጠየቅ አለባው” በማለት አሳስቧል።
የአፍሪካ ኅብረት የፕሪቶሪያ ስምምነት ትግበራን የሚቆጣጠርበትን አሠራር በመጥቀስ “የግዳጅ አፈሳውን እና የቀድሞ ተዋጊዎች ዳግመኛ መሰማራትን” መርምሮ ግኝቱን ለሕዝን ይፋ እንዲያደርግ ጠይቋል።
የሂውማን ራይትስ ዋች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ላቲሻ ባድር “የትግራይ አስተዳዳሪዎች ተጋላጭ የሆነው የትግራይ ሕዝብ ወታደራዊ ዓላማውን እንዲደግፍ በማስገደድ ለተጨማሪ ብዝበዛ ማጋለጥ የለባቸውም” ብለዋል። “የሚመለከታቸው መንግሥታት ያላቸውን ተጽዕኖ የማሳደር አቅም በመጠቀም አዲስ ግጭት እንዳይነሳ ማገዝ አለባቸው” ሲሉም አክለዋል።














