የተመድ ዋና ፀሀፊ ለቀድሞዋ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት አዲስ ሹመት ሰጡ፡፡ የቀድሞዋ የኢትዮጵያ ፕሬዝደንት ወይዘሮ ሳህለወርቅ ዘውዴ በተመድ ዋና ፀሀፊ ሀላፊነት እንደተሰጣቸው ተዘገበ፡፡
ዋና ፀሀፊው አንቶኒዮ ጉተሬዥ የሰጧቸው ይህ ሹመትም የተመድ የምእራብ አፍሪካና ሳህል ቢሮ ውስጥ ገለልተኛ ስትራቴጂያዊ ግምገማ እንዲያደርጉ የሚያስችል ነው፡፡
የተመድ የምእራብ አፍሪካና ሳህል ቢሮ በአካባቢው ለሚፈጠሩ ቀውሶች ዘገምተኛ ምላሽ በመስጠት ትችት የሚቀርበበት ሲሆን ወይዘሮ ሳህለወርቅ የተሰጣቸው ሀላፊነት የተቋሙን የአሰራር ክፍተት መመርመር ነው፡፡
ይህ የያዝነው የፈረንጆች ወር ማለትም ጁን ሲያበቃ አዲሱን ሀላፊነታቸውን የሚረከቡት የቀድሞዋ ፕሬዝደንት በመጀመሪያ ወደኒውዮርክ በማቅናት ከፀጥታው ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ እንደሚሰጣቸው ተገልጿል፡፡
በመቀጠልም የተመድ የምእራብ አፍሪካና ሳህል ቢሮ ዋና መስሪያ ቤት ወደሚገኝበት ዳካር በመጓዝ ከሴኔጋል ከፍተኛ አመራሮች ጋር በመወያየት ወደስራ የሚገቡ ይሆናል፡፡
ለወይዘሮ ሳህለወርቅ ይህ ሀላፊነት ሊሰጣቸው የቻለው ቀደም ሲል በሴኔጋል፣ ማሊ፣ ጊኒና ኬፕ ቨርዲ የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን በመስራታቸው ስለቀጠናው የተሻለ እውቀትና ግንዛቤ አላቸው በሚል ነው ፡፡














