በአዲስ አበባ ከተማ፣ ፒያሳ አካባቢ የሚገኙ እና ዕድሜያቸው ከ70 እስከ 100 ዓመት የሚጠጉ በቅርስነት የተመዘገቡ ህንጻዎች ፈረሱ። የፌደራል የቅርስ ጥናት እና ጥበቃ ባለስልጣን በበኩሉ “ሲኒማ አምፒርን” ጨምሮ የፈረሱት ህንጻዎች “የቅርስ መመዘኛ መስፈርቶችን የሚያሟሉ አይደሉም” ብሏል።
በመዲናይቱ አራዳ ክፍለ ከተማ ከፈረሱ ህንጻዎች መካከል ሸዋ ሆቴል፣ በስተኋላ ላይ ወደ ሄርሞን ሆቴል የተለወጠው የአጼ ኃይለ ሥላሴ በጎ አድራጎት ድርጅት ህንጻ እንዲሁም ቢያድግልኝ ሆቴል ይገኙበታል። ከእነዚህ በተጨማሪ የወርቅ፣ የልብስ እና የህንጻ መሳሪያዎች መሸጫ ሱቆችም መፍረሳቸው ታውቋል። ህንጻዎቹ የፈረሱት ከሁለት ቀናት በፊት ቅዳሜ ሰኔ 27፤ 2018 እንደሆነ የዓይን እማኞች እና በአካባቢው ሱቆች የነበራቸው ባለቤቶች ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ተናግረዋል።
ከፈረሱት የወርቅ ቤቶች በአንዱ የሚሰሩ ግለሰብ፤ እርሳቸው የሚሰሩበት መሸጫ ሱቅ የሚገኝበት “ሸዋ ሆቴል” በመባል የሚታወቀው ህንጻ እንደሚፈርስ ከአንድ ወር በፊት ተነግሯቸው እንደነበር ገልጸዋል። እኚሁ ግለሰብ ከወራት በፊት የኪራይ ውል ለማደስ ወደ ፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በሄዱበት ወቅት፤ ህንጻው የሚፈርስ በመሆኑ እስከዚያው ድረስ የወር ኪራይ እንዲከፍሉ እንደተነገራቸውም ጨምረው አስረድተዋል።
ዕድሜ ጠገቡ “ሸዋ ሆቴል” እንዲፈርስ የተወሰነው፤ በአጠገቡ ለተገነባው ዘመናዊ ህንጻ ማስፋፊያ እንዲውልና የህንጻውን ውበት እንዳይሸፍን ተብሎ መሆኑን እንደተነገራቸውም አመልክተዋል። እርሳቸው የጠቀሱት ህንጻ፤ ከአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ፊት ለፊት ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ ያለውን “አራዳ ሌግዠሪ ሞልን” ነው።
በገበያ ማዕከሉ አቅራቢያ ያሉ ህንጻዎች እና ሱቆች ላይ ከትላንት በስቲያ የተወሰደው የማፍረስ እርምጃ፤ “ድንገተኛ እንደሆነባቸው” በወርቅ መሸጫ ሱቁ የሚሰሩት ግለሰብ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ገልጸዋል። በአካባቢው የሚሰሩ ሌላ ግለሰብ፤ ባለፈው ቅዳሜ በሸዋ ሆቴል ውስጥ በመዝናናት ላይ የነበሩ ሰዎች እንዲወጡ ተደርጎ ህንጻው መፍረሱን ሰምቼያለሁ ብለዋል።
“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ያነጋገረቻቸው በዚያው አካባቢ ያሉ ሌላ ግለሰብ በበኩላቸው፤ የህንጻዎቹን መፍረስ በተመለከተ የአካባቢው ነጋዴዎች ቀደም ብሎ መረጃው ደርሷቸውእንደነበር ከራሳቸው አንደበት መስማታቸውንም ተናግረዋል። ከሁለት ሳምንት በፊት በስፍራው የሚገኝ አንድ የጫማ መደብር ሰራተኞች ዕቃዎቻቸውን ሲያጓጉዙ መመልከታቸውን ጠቁመዋል።
ባለፈው ቅዳሜ በስፍራው እንደነበር የገለጸ ሌላ የዓይን እማኝ፤ በዕለቱ ሲኒማ አምፒርን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ መደብሮች ዕቃ ሲያወጡ በተመሳሳይ መመልከቱን ማረጋገጫ ሰጥቷል። በትላንትናው ዕለት ወደ ቦታው ሲመለስ በአካባቢው የነበሩ ህንጻዎች ፈርሰው ማየቱንም የዓይን እማኙ አክሏል።
በሁለት ሄክታር ሜትር ስፋት ላይ የተንጣለለው የገበያ ማዕከሉ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አቶ ማናዬ ሰንደቁ ከተባሉ ባለሃብት ጋር በአጋርነት የሚያስገነባው እንደሆነ ከአንድ ዓመት በፊት ተገልጾ ነበር። ግንባታው በከተማይቱ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጭምር በየጊዜው ክትትል ሲደረግበት የቆየው የገበያ ማዕከሉ፤ ዓለም አቀፍ ብራንድ ያላቸው ዕቃዎች የሚሸጡበት እንደሆነ ተነግሯል።
በሳምንቱ መጨረሻ በህንጻዎቹ ላይ የተካሄደው የማፍረስ እርምጃ፤ ከሁለት ዓመት በፊት በፒያሳ እና በአራት ኪሎ አካባቢዎች በርካታ የንግድ ሱቆች እና የመኖሪያ ቤቶች እንዲፈርሱ ካደረገው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተደረገ ነው። በወቅቱ በአካባቢው “በቅርስነት ተመዘግበው” የነበሩ ህንጻዎች መፍረሳቸው፤ ከስነ ህንጻ ባለሙያዎች እና ከቅርስ ተቆርቋሪዎች ከፍተኛ ትችት አስከትሎ ነበር።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ በሰጡት መግለጫ፤ በአካባቢው ላይ ያሉ ቅርሶች “በጥናት መለየታቸውን” ገልጸው ነበር። “ቅርስ ህግ አለው። እንደ ፌደራል የቅርስ ባለስልጣን አለ። የከተማችን ባህል እና ቱሪዝም ቅርስን ይንከባከባል፤ ቅርስን ይጠብቃል። እነኚህን አካተናል” ሲሉ ከንቲባዋ በወቅቱ ተናግረዋል።
“እነ ሲኒማ ኢትዮጵያን፣ እነ ሀገር ፍቅርን፣ ሲቲ ኮንቬንሽንን፣ የእነ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴን ቤት፣ የቀድሞ ማዘጋጃ [ቤትን] እነኚህን እና የመሳሰሉትን ባሉበት ነው የምናድሰው። እዚህ አካባቢ ሲኒማ ሲያይ የነበረው፣ በጎልማሳነትም ሆነ በእርጅና ዕድሜ ውስጥ ያለው፣ የዛሬው ወጣትም ይገናኝበታል። ይሄንን በምንም አይነት ማህበረሰባችንን አናሳጣም። የበለጠ ሳቢ፣ ዘመኑን የሚመጥን አድርገን፣ አድሰን በቅርብ ቀን ለአገልግሎት ክፍት የምናደርጋቸው ነው የሚሆኑት” ሲሉም አዳነች በዚሁ መግለጫቸው ተናግረዋል።














