Image

በርካታ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የሚገኙባት ሳዑዲ አረቢያ ከጥር እስከ ሰኔ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ሰባት ኢትዮጵያውያንን በሞት መቅጣቷን ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ከሦስት ሳምንት በፊት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

ሐሚስ ሙሻይት በተባለው እስር ቤት ብቻ ቢያንስ 63 ኢትዮጵያውያን ደግሞ የሞት ፍርድ ተላልፎባቸው እየተጠባበቁ መሆኑን አምነስቲ እና ሌላኛው ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ገልጸዋል።

ሲኤንኤን (CNN) አዲስ ባወጣው የምርመራ ዘገባ በሳዑዲ ዓረቢያ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸውን ኢትዮጵያውያን ስደተኞች አሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ መሆናቸውን አመላክቷል። በደርዘን የሚቆጠሩ ስደተኞች ከዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ተከሰው በከባድ ማሰቃየት፣ ፍትሐዊ ባልሆነ የፍርድ ሂደት እና የሕግ ጠበቃ በሌለበት የሞት ፍርድ እንደተበየነባቸው ዘገባው አመልክቷል።

ዘገባው ትኩረቱን ያደረገው በደቡብ ምዕራብ ሳዑዲ ዓረቢያ ኸሚስ ሙሻይት እስር ቤት ውስጥ በሚገኝ አንድ ኢትዮጵያዊ የሕይወት ታሪክ ላይ ነው። ማንነቱን ላለመግለጽ «አማኑኤል» በሚል ስም የተጠቀሰው ይህ ወጣት በሰሜን ኢትዮጵያ ተከስቶ ከነበረው ግጭት (በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት) ከትግራይ ክልል በመሸሽ በየመን በኩል የተሰደደ ሲሆን፥ በኋላም በሳዑዲ ዓረቢያ በእረኛነት ተቀጥሮ ሲሠራ ቆይቶ ሐሺሽ በማዘዋወር ወንጀል በቁጥጥር ሥር ውሏል።

አማኑኤል ለሚዲያው እንደተናገረው፥ በምርመራ ወቅት ድብደባ እንደተፈጸመበት፣ ሊረዳቸው የማይችላቸውን በአረብኛ የተጻፉ ሰነዶችን በግድ እንዲፈርም መደረጉን፣ ጠበቃም ሆነ የኢትዮጵያ ቆንስላ ባለሥልጣናትን የማግኘት መብት እንደተከለከለ እና የሞት ፍርድ ከመፈረዱ በፊት በጣም አጭርና ውስን የትርጉም አገልግሎት ብቻ የነበረው የፍርድ ቤት ችሎት እንደተደረገ ገልጿል።

«እኔ በሕይወት ያለሁ ሙት ነኝ» ሲል ለሚዲያው የተናገረው ወጣቱ፥ በአንድ ክፍል ውስጥ አብረውት የነበሩ አምስት እስረኞች በቅርቡ ያለምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ መገደላቸውን ተናግሯል።

በተጨማሪም በፍርሃት ውስጥ እንደሚኖር፣ የሞት ፍርዱን በኢትዮጵያ ከሚገኙ ቤተሰቦቹ እንደደበቀ እና ክርስቲያን በመሆኑ ሃይማኖታዊ መድልዎ እየደረሰበት መሆኑን ገልጿል። ዘገባው በርካታ እስረኞች ራሳቸውን ለማጥፋት ሙከራ አድርገዋል ሲል ገልጿል።

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እንደገለጹት፥ በኸሚስ ሙሻይት እስር ቤት ብቻ ከዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች ምክንያት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው የኢትዮጵያ ዜጎች ቁጥር 60 ገደማ እንደሚሆን የሚታመን ሲሆን፥ በሌሎች ተቋማት ውስጥም በተመሳሳይ የፍርድ ውሳኔ የተያዙ ተጨማሪ ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ።

ዘገባው እንዳመለከተው ሳዑዲ ዓረቢያ እ.እ.አ በ2025፤ በ356 ሰዎች ላይ የሞት ፍርድ የፈጸመች ሲሆን፥ ይህም በቅርብ ዓመታት ውስጥ ከተመዘገቡት የሞት ፍርድ ከፍተኛው ቁጥር ነው። ከእነዚህ ውስጥ 240 የሚሆኑት ከዕፅ ጋር በተያያዙ ወንጀሎች የተፈረደባቸው ሲሆን፥ አብዛኛዎቹ የውጭ ሀገር ዜጎችን ያካተቱ ናቸው።

እ.እ.አ. በ2026፤ 71 ሰዎች ለሕይወት አስጊ ባልሆኑ የዕፅ ወንጀሎች የሞት ፍርድ የተፈጸመባቸው ሲሆን፥ ለእነዚህ ወንጀሎች የሞት ፍርድ ከተፈጸመባቸው የውጭ ሀገራት ዜጎች መካከል ከፍተኛውን ቁጥር ኢትዮጵያውያን እንደሚይዙ የምርመራው ውጤት ያሳያል።

ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው የሕግ ባለሙያዎች እና የመብት ተሟጋቾች እንደተናገሩት፥ በርካታ ተከሳሾች ሥርዓታዊ የሆኑ እንቅፋቶች ይገጥሟቸዋል። ከእነዚህም መካከል ብቁ የሕግ ጠበቃ አለማግኘት፣ በቂ ያልሆነ የትርጉም አገልግሎት እና በማሰቃየት የተገኙ የእምነት ቃሎችን መሠረት በማድረግ የሚሰጡ የጥፋተኝነት ውሳኔዎች ይገኙበታል። መደበኛ ባልሆኑ መንገዶች የሚጓዙ ስደተኞች በተለይ በአሸጋጋሪዎች እና በወንጀል መረቦች ለብዝበዛ የተጋለጡ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህ ምርመራ ዘገባ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በጅቡቲ እና በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ ለሥራ ፍለጋ የሚጓዙበትን የፍልሰት መስመር አደገኛነት የሚያመላክት ሲሆን፥ ስደተኞች በዚህ መስመር ለዘረፋና ለዕገታ እንደሚጋለጡ እንዲሁም ሕገ-ወጥ ዕቃዎችን እንዲያጓጉዙ በአዘዋዋሪዎች ግፊት ይደረግባቸዋል ተብሏል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 6/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ፤ “መንግሥት በውጭ አገር ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን ደህንነት፣ ጥበቃ እና የቆንስላ እገዛ ትልቅ ቦታ እንደሚሰጥ” ጠቅሷል። ከዚህ ጋር በተያያዘ መንግሥት “የሕግ ሂደት ላይ የሚገኙ እና የፍርድ ውሳኔ የተላለፈባቸው” ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ ከሳዑዲ ጋር “በከፍተኛ የመንግሥት ተቋም ደረጃ መነጋገር እንደቀጠለ” ገልጿል።

በተጨማሪም ሪያድ ውስጥ በሚገኘው ኤምባሲ እና በጅዳ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት አማካኝነት “አስቸጋሪ ሁኔታዎች ለገጠሟቸው ኢትዮጵያውያን ዜጎች ሰብአዊነትን ከግምት ያስገባ” እርምጃ እንዲወሰድ የሚደረገው ጥረት መቀጠሉን ገልጿል።

በዲፕሎማሲያዊ ቢሮዎቹ አማካኝነት ኢትዮጵያውያኑ “የቆንስላ ድጋፍ እንዲያገኙ ለማድረግ እና ተገቢውን መፍትሔ ለማስገኘት ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ባለሥልጣናት ጋር መደበኛ ግንኙነት እና ገንቢ ውይይት” እየተካሄደ መሆኑንም ጠቅሷል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ እንደሚገልጸው፤ መንግስት ያደረጋቸው ጥረቶች ሳዑዲ ውስጥ ፍርድ የተላለፈባቸው በአጠቃላይ 1,971 ኢትዮጵያውያን ንጉሳዊ ምሕረት እንዲያገኙ አስችለዋል። እነዚህን ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የመመለስ ተግባር መጀመሩንም በመግለጫው አንስቷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኢትዮጵያውያኑ ምህረት እንዳገኙ ከአንድ ወር በፊትም አስታውቆ ነበር። መስሪያ ቤቱ ይህንን በገለጸበት ሳምንት ደግሞ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት አራት ኢትዮጵያውያን ላይ የሞት ፍርድ መፈጸሙን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በግንቦት 2018 ዓ.ም ካካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ በኋላ፥ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ «ሰብአዊ መብትን፣ ምሕረትን እና ፍትሕን» እንዲያስከብሩ ጠንካራ ጥሪ አቅርቧል።

ሲኖዶሱ በውጭ ሀገራት የሚገኙ የኢትዮጵያውያንን መብትና ክብር ለመጠበቅ የተቀናጀ ጥረት እንዲደረግ አጥብቆ አሳስቧል። በተመሳሳይ መልኩ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያ ጳጳሳት በግንቦት 2018 ዓ.ም ባወጡት መልዕክት፥ የሳውዲ አረቢያ መንግሥት በኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ ያስተላለፈውን የሞት ፍርድ እንዲያነሳ ጠይቀዋል።

እንግሊዝ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስጠነቀቀች

እንግሊዝ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስጠነቀቀች

ሻዕቢያን ከሳህል በረሃ የትጥቅ ትግል ዘመን ጀምሮ ኤርትራን ገንጥሎ መንግስት እስከሚሆን ድረስ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት አጋር ሆነው የፋይናስና…

ጥቅም 15, 2026
ኦነግ ለኢሳይያስ ንግግር በመግለጫ ምላሽ ሰጠ

ኦነግ ለኢሳይያስ ንግግር በመግለጫ ምላሽ ሰጠ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትናንት ባወጣው መግለጫ “ህዝባችን ላይ የታወጀና በቀጣናው ደግሞ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እየጠነከሩ በመምጣታቸው እንዲሁም…

ጥቅም 14, 2026
የተቋረጠው የትግራይ በረራ በድጋሚ መጀመሩ ምን ያመለክታል?

የተቋረጠው የትግራይ በረራ በድጋሚ መጀመሩ ምን ያመለክታል?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜያዊነት ተቋርጦ የነበረውን ወደ መቀሌ ከተማ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ እሁድ ከጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ…

ጥቅም 12, 2026
ኢትዮጵያ ስለተፈጸመባት ወረራ ለተመድ የፀጥታ ም/ቤት አሳወቀች

ኢትዮጵያ ስለተፈጸመባት ወረራ ለተመድ የፀጥታ ም/ቤት አሳወቀች

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት…

ጥቅም 12, 2026