በኢራን የሚደገፉት የየመን ሁቲ ኃይሎች የሳውዲ አረቢያ መርከቦች የባሕር እንቅስቃሴ ላይ እገዳ አወጁ። ቡድኑ እገዳውን ያወጀው ሳውዲ አረቢያ በየመን ላይ ” ኢፍትሃዊና ጨቋኝ ከበባ እየጣለች ” በሚል ክስ ነው።
የቀይባሕር ዋነኛ መተላለፊያ የሆነው የባብ አል-መንደብ ሰርጥ ለሳውዲ መርከቦች እንደሚዘጋ ሁቲዎች አስታውቀዋል። ይህ ከ2022 ጀምሮ በተመድ ድጋፍ ሲቆይ የነበረውን የተኩስ አቁም ስምምነት የሚያዳክም እርምጃ መሆኑ ተጠቁሟል።
እገዳው የመጣው በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባለው የሰነአ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ከተፈጸመ ጥቃት በኋላ ነው። የየመን መንግሥት የኢራን አውሮፕላን እንዳያርፍ ለመከላከል “ጥቃቱን ፈጽሜያለሁ” ቢልም፤ ሁቲዎች ግን ሳውዲን ተጠያቂ በማድረግ የሚሳይል ጥቃት ከፍተው አሁን ደግሞ የባሕር ላይ እንቅስቃሴ እገዳ አውጀዋል።
ባብ አል-መንደብ ሙሉ በሙሉ ከተዘጋ የዓለም የነዳጅ አቅርቦት እስከ 7 በመቶ ሊቀንስ፤ በቀይ ባሕር የሚካሄደውን የንግድ መጓጓዣ እና የኃይል አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ ሊያውክ ይችላል።
በሌላ በኩል፤ ሳውዲ አረቢያ እንዲሁም በሳውዲ የሚመራው ጥምረት የሁቲዎችን መግለጫ “አሳሳች” በማለት ውድቅ አድርገውታል። በሁቲዎች ቁጥጥር ስር ባሉ ወደቦች በመቶዎች የሚቆጠሩ የንግድ መርከቦች አሁንም ያለ እንቅፋት እየገቡና እየወጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ጥምረቱ የሁቲዎች የባሕር እገዳ ውሳኔን ” የዓለም አቀፍ ህግ የሚጥስ የባሕር ወንበዴነት ተግባር ” ሲል በማውገዝ፣ በባብ አል-መንደብ ባሕረ ሰላጤ የሚያልፉ የሳውዲ የንግድ መርከቦችን ለመጠበቅ የደህንነት ጥበቃ እርምጃዎችን መጀመሩን አስታውቋል።
ከየመን የሁቲ ኃይሎች ጀርባ ኢራን ግፊት እያደረገች መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የየመን ሁቲዎች የባሕር ላይ እንቅስቃሴ እገዳ በቀጠናው እየተባባሰ ካለው የጂኦፖለቲካ ውጥረት ጋር የተያያዘ መሆኑም እየተነገረ ነው።
ኢራን በመሠረተ ልማቶቿ ላይ ለሚፈጸመው የአሜሪካና የእስራኤል ወታደራዊ ጥቃት ምላሽ እንዲሆን፣ ሁቲዎች የምዕራባውያንና የባሕረ ሰላጤ ሀገራት የመርከብ መጓጓዣ ወሳኝ መተላለፊያዎችን እንዲያውኩ “ግፊት አድርጋባቸዋለች” ተብሏል።














