በራያ አላማጣ ከተማና አካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞችና አረብ ሃገራት በስደት እያመሩ መሆኑን ገለጹ። ወጣቶቹ ህወሓት በትግራይ ዳግም ጦርነት ሊቀሰቀስ ይችላል የሚል ሥጋት ገብቷቸዋል ፤ በፖለቲካ አመለካከታችንም ለእስር እየተዳረግን ነው ሲሉ አመልክተዋል።
የአላማጣ ከተማ አስተዳደር በአካባቢው ሰላም በመስፈኑና ወደ ተረጋጋ ሁኔታ በመመለሱ ተሰድደዉ የነበሩ ወጣቶች ወደ ቀዬያቸው እየተመለሱ ነው ቢልም፣ ወጣቶች ግን አሁንም ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ዓረብ ሃገራት መሰደድ መቀጠላቸውን እየገለጹ ነው።
በአላማጣ ከተማና አካባቢው የሚገኙ ወጣቶች ዳግም ጦርነት ሊከሰት ይችላል በሚል ስጋትና ባላቸው የፖለቲካ አመለካከት ለእስር እየተዳረግን ነው በሚል ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እየተሰደዱ መሆኑን ተናገሩ። የወጣቶቹ መሰደድ በፈጠረው ማኅበራዊ ቀውስ ምክንያት ወጣቶች በፀጥታ ኃይላት እንዳይያዙ በመስጋት ወላጆቻቸው ሲሞቱ በቀብር ስነ ስርዓታቸው ላይ ጭምር መታደም አለመቻላቸውንም ነው የሚናገሩት።
«ፈተናው በጣም በጣም የበዛ የበዛ… እናት አባትህን አያስቀብር፣ የእናት ልጅህን አያስቀብር። ይኸው ትላንትና የሞተው አባቴ ዛሬ እየተቀበረ ነው ያለው፤ እኔ ግን መሄድ አልችልም፤ ተሰድደን በየሰው ሀገር። ከዚህ መርሮት ቆቦ ይሄዳል፣ ከቆቦ መርሮት ወልዲያ ይሄዳል፣ ከወልዲያ መርሮት ደሴ ይሄዳል፣ ከደሴ አዲስ አበባ፣ ከአዲስ አበባ ጅዳ ይገባል፣ ባህር እየገባ በባህር በዓሣ እየተበላ ነው ያለው የእኛ ተወላጅ። በተለይ የራያ ግፍና መከራ በጣም በዝቶብናል ወንድም። እኛ በቃ እዚህ ቆቦ ነው ያለን አሁን ለምሳሌ፣ ቆቦ ላይ ሆነን በቃ ስጋት ነው ያለን።»
በተለይም በአላማጣ ከተማ የሚገኙ ወጣቶች ከፍተኛ ገንዘብ በማውጣት ጭምር አካባቢያቸውን እየለቀቁ በህገ-ወጥ መንገድ ወደ አረብ ሃገራት የሚያደርጉት ጉዞ አሁንም መቀጠሉ ይገለጻል። «ቤት ንብረቱን ሽጦ ወደ ሳውዲ ይሄዳል፣ በሊቢያ ይሄዳል፤ እስከ ሁለት ሚሊዮን፣ ሦስት ሚሊዮን አውጥቶ ይሄዳል፤ ያ ደግሞ ሳይሳካ ሲቀር ደግሞ ራሱን ያጠፋል።
ግማሹ በጣም ብዙ ወጣት እኮ ነው፣ በጣም ብዙ! እንጂ አሁን ደግሞ የባሰ ነው፣ ከዛኛው እንደውም ይብሳል ተብሎ ነው የሚጠበቀው አሁን። ወጣት እኮ የለም አሁን እዛ ያሉት አሮጊት እናቶች ብቻ ናቸው እዛ ያሉት።»
አካባቢያቸውን ለቀው የሚሰደዱ ወጣቶች አብዛኞቹ የአረብ ሀገራትን መዳረሻ ማድረጋቸው ለከፋ ችግር ዳርጓቸዋል ይላሉ የቀድሞ የአላማጣ ከተማ አስተዳዳሪ የነበሩት አቶ ስዩም አርብሴ። «አዎ፤ አላማጣ በጣም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለው ማህበረሰቡ።
የስራ እድልም የለም፤ በዚህ ሰዓት የጅዳ በረሃ እየበላው ያለው፣ የጅዳ በረሃ ሊቢያ እስር ቤት ላይ እየተቃየ ያለው የራያ ሰው ነው። ሁኔታዎች በጣም ከባድ ናቸው፣ በጣም አሳዛኝ።»
ገና ለገና ጦርነት ሊፈጠር ይችላል የሚል ግምት ይዘው አካባቢያቸውን ለቀው በሀገር ውስጥም ወደ ውጭም የሚሰደዱ ወጣቶች መኖራቸው እውነት ነው የሚሉት የአላማጣ ከተማ ከንቲባ አቶ ሞገስ ሽፈራው፣ ይሁን እንጂ አሁን ላይ አካባቢው ሰላማዊ በመሆኑ ቀደም ሲል ሸሽተው የወጡ ወጣቶች እየተመለሱ ነው ሲሉ ይናገራሉ።
«ወጣቱ ጦርነት ሊፈጠር ይችላል የሚል የቅዠት ፕሮፓጋንዳ እየሰሙ ከዚህ ወደ አረብ ሀገር ብቻ ሳይሆን ወደ አዲስ አበባም ወደ ተለያዩ ቦታ ሊሄድ ይችላል። አሁን ደግሞ እኛ አካባቢ ያለው የሰላም ሁኔታ ከተረጋጋ በኋላ እንደ አዲስ ወደ ቤቱ መመለስ ጀምሯል። ወደ ቤቱ እየተመለሰ ነው ያለው፣ እቤቱም እየገባ ነው ያለው። እኛም ወደ ቤቱ በመመለሱ ደስተኞች ነን።»
በአላማጣ ከተማ ከሰሜኑ ጦርነት በኋላ ለወጣቶች የተፈጠረው የስራ እድል አነስተኛ ነበር የሚሉት አቶ ሞገስ፣ አሁን ላይ መንግስት የተለያዩ የስራ እድሎችን መፍጠሩን ይገልጻሉ።
«የሥራ እድል ሊፈጠር የሚችለው አንዱ በመንግስት ደረጃ ነው፣ ሁለተኛ ደግሞ በግለሰብ ደረጃ ነው። በግለሰብ ደግሞ የግል ተቋማት ስራ ክፍት ከሆኑ፣ አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ የስራ እድል ይፈጠራል።
መንግስት እንደ መንግስት ደግሞ ተቋሙን ከፍቶ ወደ ስራ ከገባ የስራ እድል ሊፈጥርላቸው የሚችሉ አጋጣሚዎችን መፍጠር ይችላል ማለት ነው። የስራ እድል ግን እንደምታውቀው… ትክክል ነው፣ ሰፊ የስራ እድል እጥረት ነበረ። አሁን ግን በውስን መንገድ ሰዎች በሚያደርጉት እንቅስቃሴ፣ መንግስት በሚያደርገው እንቅስቃሴ የስራ እድል እየተከፈተ ነው ማለት ይቻላል።»
ምንም እንኳን የአላማጣ ከተማ አስተዳደር ወጣቶች ከዚህ ቀደም ጦርነትን ሽሽት ከሄዱበት እየተመለሱ ነው ቢልም፣ በኬላዎች ላይ በሚደረግ ጥብቅ ፍተሻ ተፈላጊ ወጣቶች እየተያዙ ነው ተብሏል።
ህወሓት ለዳግም ጦርነት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አስመልክቶ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣናት እና የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በስፋት ሲወነጅሉ፣ የቡድኑ አመራሮች ግን የትግራይን ሕልውና ለመከላከል የሚደረግ ዝግጅት እንጂ ጦርነት ፈላጊ እንዳልሆኑ በመግለጽ ውዝግብ ውስጥ ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ፤ የህወሓት አመራር “ሰፊ ወታደራዊ ዝግጅት”፣ “የጦር መሣሪያ ግዥ” እና “ወታደራዊ ቅስቀሳዎችን እያደረገ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ በፌደራል መንግሥት በኩል አስገዳጅ ሁኔታ እስካልተፈጠረ ድረስ በጭራሽ ትግራይ ላይ የሚጀመር ጦርነት እንደማይኖርም ማረጋገጫ ሰጥተዋል፡፡
የፌደራል መንግሥት በፕሪቶሪያው ስምምነት የተጣሉበትን ግዴታዎች “እንደፈጸመ” የገለጹት ዐቢይ፤ “አሁን ችግር ሆኖ ያለው ከወልቃይት አካባቢ የተፈናቀሉትን [ነዋሪዎች] የሚመለከት ነው” ብለዋል።
“ይህ ደግሞ ግትር አቋም ባለው ቆሞ ቀሩ ኃይል ምክንያት አልተሳካም” ሲሉ በህወሓት ውስጥ ይገኛል ያሉትን ቡድን ተጠያቂ አድርገዋል። “ብዙ ጊዜ ተነጋግረናል አሁንም እምነታችን ምን እንደሆነ ሕዝባችን ያውቀዋል። ነገር ግን በቆሞ ቀሩ ግትር አቋም ምክንያት ያሰብነው ሊሳካ አልቻለም” ሲሉም ተናግረዋል።
በፕሪቶሪያው ስምምነት ውስጥ “ትልቁ የቤት ሥራ” ብለው የሚወስዱት “ከወልቃይት የተፈናቀሉ” ነዋሪዎችን ጉዳይ እንደሆነ ያነሱት ዐቢይ፤ “ተፈናቃዮች የግድ ወደ ቦታቸው መመለስ አለባቸው” ሲሉ ተደምጠዋል።
የሁለት ዓመቱን ጦርነት ያስቆመው የፕሪቶሪያ ስምምነት “በሙሉነት እንዳይፈጸም” ምክንያት ከሆኑ አንዱ “ህወሓት ሕገ መንግሥቱንና ተቋማትን ባለማክበር ወደ ጎን” መተዉ እንደሆነም በማንሳት ወቅሰዋል።














