Image

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሰራር ላይ ያነሳችው አዲስ ውንጀላ ኢትዮጵያ ግድቡን ለፖለቲካ ፍጆታ እየተጠቀመችበት ነው የሚል ሲሆን፣ ይህ ከግንባታ መጀመር አንስቶ በተባበሩት መንግስታት የጸጥታ ምክር ቤት እና በሌሎች ዓለም አቀፍ አካላት ሲቀርብ የቆየው ተከታታይ ክስ አንድ አካል ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

ግድቡ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የሰሞኑን ክስ ሳይጨምር ግብፅ ጉዳዩን ወደ የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ምክር ቤት፣ ለዓረብ ሊግ እና ለተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች ከአምስት ጊዜ በላይ በይፋዊ ደብዳቤዎች አቤቱታ አቅርባለች። ኢትዮጵያ ግድቡን መርቃ አገልግሎት ማስጀመሯን ተከትሎም ካይሮ ተቃውሞዋን በማጠናከር በተደጋጋሚ የማስፈራራትና የክስ መዝገብ የመክፈት ሄደቷን አላቋረጠችም።

የኢትዮጵያ የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ ሰሞኑን ግብፅ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያቀረበችውን “መሰረተ ቢስ ውንጀላ” ውድቅ ያደረጉ ሲሆን፣ ካይሮ በፕሮጀክቱ ላይ እውነታውን ያላገናዘቡ አቤቱታዎችን ከመደርደር ይልቅ ቀደም ሲል በተስማሙባቸው ማዕቀፎች መሠረት ወደ ድርድር ብትመለስ የበለጠ ተጠቃሚ እንደምትሆን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ሐምሌ 21 ቀን 2018 ዓ.ም ለፋና ሚዲያ በሰጡት መግለጫ፣ የፓን-አፍሪካኒዝም እና የራስን እድል በራስ የመወሰን ተምሳሌት እንደሆነ የሚገለፀው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ለታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት “ከስጋት ይልቅ በረከት” ተደርጎ ሊወሰድ እንደሚገባው ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ፕሮጀክቱ ምንም ዓይነት ጎልቶ የሚታይ ጉዳት አላደረሰም የሚሉ ማስረጃዎችን ብታቀርብም፣ ግብፅ ግን ግድቡ በሚገነባበት ወቅትም ሆነ ከተጠናቀቀ በኋላ ውንጀላዋን ከመሰንዘር አልተቆጠበችም።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ለማሟላት በሀገር ውስጥ ሀብት በገንዘብና በጉልበት የገነባችውን ግድብ ግብፅ “የደህንነት ስጋት” አድርጋ ማቅረቧ አቅጣጫውን የሳተ ነው ብለዋል። በተጨማሪም ህዳሴ ግድቡ ለሱዳን፣ ለጂቡቲ እና ለኬንያ ኤሌክትሪክ በመላክ ቀጣናዊ ትስስርን እንደሚያጠናክር እንዲሁም በሱዳንና በግብፅ ላይ የሚከሰተውን ወቅታዊ የጎርፍ አደጋ ለመቆጣጠር እንደሚረዳ አብራርተዋል።

ሚኒስትሩ በተጨማሪም “ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በመሙላቷ እና በማንቀሳቀሷ በግብፅ የውኃ ማከማቻዎች ውስጥ ያለው የውኃ መጠን እንዲቀንስ አድርጓል” የሚለውን የግብፅ ውንጀላ “ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።

ይልቁንም ኢትዮጵያ ለቀጣናዊ ትስስር እና ለጋራ ኢኮኖሚያዊ እድገት ቁርጠኛ መሆኗን ገልጸው፣ ግብፅ መሰረተ ቢስ ውንጀላዎችን ከማስፋፋት ይልቅ በተስማሙባቸው የጋራ ማዕቀፎች ስር ብትደራደር የበለጠ እንደምትጠቀም መክረዋል። አክለውም ኢትዮጵያ እንደ አንድ ሉዓላዊ ሀገር ተፈጥሯዊ ሀብቷን የማልማትና የመጠቀም መብቷ የተጠበቀ መሆኑን አስምረውበታል።

ግብፅ በኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ የምታቀርበው ተቃውሞ ከግድቡ ጋር ብቻ የተያያዘ አይደለም፤ ይልቁንም የዓባይ ወንዝ ውሃ እንዴት ሊተዳደር እንደሚገባ በሚመለከት መሠረታዊ የአመለካከት ልዩነት ነው።

ለብዙ ዓመታት ግብፅ ሕጋዊ አቋሟን እ.አ.አ በ1929 በእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ዘመን በተፈረመው የአንግሎ-ግብፅ ስምምነት እና እ.አ.አ በ1959 በግብፅና በሱዳን መካከል በተፈረመው የዓባይ ውሃ ስምምነት ላይ መስርታለች።

ሁለቱ ስምምነቶች አብዛኛውን የዓባይ ውሃ ለግብፅና ለሱዳን ብቻ በመመደብ ሌሎችን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከሂደቱ ውጭ አድርገዋል። ኢትዮጵያ በሁለቱም ስምምነቶች ተሳታፊ ስላልነበረች ያለ ኢትዮጵያ ፈቃድና ተሳትፎ በተደረጉ ስምምነቶች በሕግም ሆነ በሥነ-ምግባር እንደማትገዛ ታስረዳለች።

ከኢትዮጵያ እይታ አንጻር በቅኝ ግዛት ዘመን የተደረጉ ስምምነቶች በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአፍሪካ ሉዓላዊ መንግሥታትን መብትና ኃላፊነት ሊወስኑ አይችሉም። አንዳንድ የግብፅ ወገኖች እነዚህ ስምምነቶች “ታሪካዊ መብት” እንደፈጠሩ ቢከራከሩም ኢትዮጵያ ይህንን ትርጓሜ አትቀበለውም።

እንደ ኢትዮጵያ ገለጻ፤ ያልተወከሉና ያልተማከሩ ሀገራትን ወክሎ የዓለም አቀፍ ወንዝ ውሃን ለመመደብ ማንኛውም የቅኝ ገዥ ኃይል ሥልጣን አልነበረውም። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ዓባይ የጋራ ዓለም አቀፍ ወንዝ በመሆኑ አስተዳደሩ በዘመናዊ የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ መርሆች ሊመራ እንደሚገባ ትከራከራለች።

እነዚህ መርሆች ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም፣ በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ትብብር እና ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ የመከላከል ግዴታን ያጠናክራሉ። በዚህ መሠረት ማንኛውም ሀገር በዓባይ ላይ ብቸኛ ባለቤትነት ወይም ፍጹም መብት የለውም፤ የአንድ ሀገር የልማት ፍላጎትም የሌሎችን ሀገሮች የልማት መብት ለዘላለም ሊገድብ አይገባም።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በዋናነት የተገነባው ለከፍተኛ የመስኖ ልማት ሳይሆን ንጹህና ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ነው። ኢትዮጵያም ፕሮጀክቱ የንጹህ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የሃገሪቱንና የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ ልማት ለማጠናከር እንዲሁም በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ትብብርን ለማሳደግ እንደተነደፈ በተደጋጋሚ ገልጻለች።

የሀገሪቱ ሕዝብ ቁጥርና የልማት ፍላጎት እየጨመረ በመሆኑ ኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ አካታችና በትብብር የተመሠረተ የውሃ አስተዳደር ሥርዓት አስፈላጊ መሆኑን ታስረዳለች።

የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት የተደራደሩበት የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት የዚህ አቀራረብ መገለጫ መሆኑንም ትገልጻለች። ስምምነቱ ፍትሐዊና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀምን በማበረታታት በተፋሰሱ ሀገራት መካከል ትብብርንና ዘላቂ የሀብት አስተዳደርን ለማጠናከር ያለመ ሲሆን ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን አጽድቀውታል።

ከኢትዮጵያ እይታ አንጻር በዓባይ ተፋሰስ ዘላቂ ሰላምና ብልጽግና የሚረጋገጠው አብዛኛዎቹን የተፋሰሱ ሀገሮች ካገለሉ የቅኝ ግዛት ዘመን ስምምነቶች በመነሳት ሳይሆን በመተማመን፣ በትክክለኛ ውይይት፣ በፍትሕ፣ በትብብር እና በዘመናዊ የዓለም አቀፍ የውሃ ሕግ መርሆች ላይ በመመስረት ነው።

ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ስምምነቶች ላይ ከመተማመን ይልቅ በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅም እና በዘላቂ ልማት ላይ የተመሠረተ የወደፊት ትብብር ላይ የተመሰረተ እንዲሆን እየሰራች ነው:: ይህም ለአሁኑም ሆነ ለሚመጡት ትውልዶች የሀገራትን መረጋጋትና ብልጽግና የሚያረጋግጥ ገንቢ መንገድ መሆኑን ታምናላች።

እንግሊዝ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስጠነቀቀች

እንግሊዝ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስጠነቀቀች

ሻዕቢያን ከሳህል በረሃ የትጥቅ ትግል ዘመን ጀምሮ ኤርትራን ገንጥሎ መንግስት እስከሚሆን ድረስ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት አጋር ሆነው የፋይናስና…

ጥቅም 15, 2026
ኦነግ ለኢሳይያስ ንግግር በመግለጫ ምላሽ ሰጠ

ኦነግ ለኢሳይያስ ንግግር በመግለጫ ምላሽ ሰጠ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትናንት ባወጣው መግለጫ “ህዝባችን ላይ የታወጀና በቀጣናው ደግሞ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እየጠነከሩ በመምጣታቸው እንዲሁም…

ጥቅም 14, 2026
የተቋረጠው የትግራይ በረራ በድጋሚ መጀመሩ ምን ያመለክታል?

የተቋረጠው የትግራይ በረራ በድጋሚ መጀመሩ ምን ያመለክታል?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜያዊነት ተቋርጦ የነበረውን ወደ መቀሌ ከተማ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ እሁድ ከጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ…

ጥቅም 12, 2026
ኢትዮጵያ ስለተፈጸመባት ወረራ ለተመድ የፀጥታ ም/ቤት አሳወቀች

ኢትዮጵያ ስለተፈጸመባት ወረራ ለተመድ የፀጥታ ም/ቤት አሳወቀች

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት…

ጥቅም 12, 2026