የቲዲኤፍ (TDF) ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ እና የትግራይ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ሌተናል ጄነራል ፍስሃ ኪዳኑ (በቅጽል ስማቸው ፍስሃ ማንጁስ) ሰሞኑን ካይሮ መሰንበታቸውንና ዛሬ ወደ ትግራይ መመለሳቸውን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች አስታውቀዋል፡፡
የህወሓት የፖለቲካ ክንፍ ከሓምሌ 27/ 2018 በኋላ “ጦርነት እንጀምራለን፤ ዝግጅታችንንም ጨርሰናል” ሲል አስታውቋል።
ከካይሮው ጉዞ ጥቂት ሳምንታት ቀደም ብሎ የቲዲኤፍ (TDF) ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ የሆኑት ሌተናል ጄነራል ፍስሃ ኪዳኑ (በቅጽል ስማቸው ፍስሃ ማንጁስ) ወደ ኤርትራ ተጉዘው እንደነበር ታውቋል፡፡
ፍሰኃ ማንጁስ ወደ ኤርትራ ያደረጉት ጉዞ ዋና ዓላማ “ፅምዶ” ከተባለውና የኢትዮጵያን ፌደራል መንግሥት ለመውጋት ከተመሰረተው አዲስ ጥምረት ጋር የተያያዘ የፖለቲካ እና የውትድርና ትብብር ለመፍጠር ነው።
የዚህ ጉዞ እና ግንኙነት ዋና ዋና ዓላማዎችና ዝርዝሮች፡ የጋራ ግንባር መፍጠር፣ በትግራይ፣ በአማራ (ፋኖ) እና በኦሮሚያ ክልል ያሉ ነፍጥ አንስተው የሚዋጉ የፖለቲካ ኃይሎችን ከአስመራ መንግሥት ጋር በማስተባበር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራውን የፌደራል መንግሥት ለመጫን ወይም ለመቃወም የተመሰረተውን ስምምነት ማጠናከር ነው።
የጦር መሣሪያና የሎጂስቲክስ አቅርቦት ማስተናገድ አንዱ የጎዟቸው አላማ ሲሆን ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመነጋገር በሱዳን በኩል ለሚንቀሳቀሱ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉት የጥምረቱ የጋራ ታጣቂ ኃይሎች የሚሆን የጦር መሣሪያ እና የሎጂስቲክስ አቅርቦት መስመሮችን የማመቻቸት ሥራ ሠርተዋል።
በሱዳን ካለው ወቅታዊ ጦርነት ጋር ተያይዞ በፖርት ሱዳን ከጄነራል አል-ቡርሃን ኃይሎች ጋር የተጀመረውን የውትድርና እና የገንዘብ ድጋፍ ስምምነት ተፈጻሚ ለማድረግ ከኤርትራ ወታደራዊ መሪዎች ጋር በቅንጅት መሥራትም ሌላው ፍሰሀ ማንጁስ ይዘው የሄዱት ተልእኮ አካል ነው።
ይህ የጄነራል ፍስሃ ማንጁስ እና የኤርትራ ግንኙነት በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ውስጥ በነበሩት አመራሮች በተለይም በጌታቸው ረዳ እና በጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳኤ ዘንድ “ክልሉን ወደ አዲስ ግጭት የሚያመራ አካሄድ ነው” በሚል ከፍተኛ ተቃውሞና በፓርቲው ህወሓት ውስጥ ለተፈጠረው መከፋፈል አንዱ ትልቅ ምክንያት ሆኖ ቆይቷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሻዕብያ ሶስት ሬጅመንት መካናይዝድ ጦር ወደ ደቡብ ትግራይ ይገባና ያግዘናል በማለት ህወሓት በእነዚህ ኃይሎች ድጋፍ ላይ የተማመነ ይመስላል።
ይህንኑ ከግምት ውስጥ በማስገባት በምዕራብ ግንባር ያለውን ኃይል ወደ ተከዘ አከባቢ ማስጠጋት ይዟል።
ፀጋይ ማርክስ የሚባለው ግን “እኛ አቅም የለንም። የፓለቲካ መሪዎች ጦርነት ይጀመር እያሉ ነው ምን እንደሚያመጡ እናያለን” በማለት ፍርሃቱንና ብስጭቱን ገልጿል። በፊትም ሰሜን እዝን ቀድመን ስናጠቃ ይኸው የፖለቲካ አመራር ለስልጣን ብሎ በማያውቀው የጦርነት ትንተና ተመስርቶ በሰጠው ውሳኔ ነበር ያን ሁሉ ኪሳራ የተከናነብነው ሲል ሁኔታውን በምሬት ገልጿል።
“የአሁኑ ግን ከበፊቱም የከፋ ነው” በማለት ነቀፌታ እያቀረበ ይገኛል።
በግዳጅ የታፈሱት አዲስ ምልምሎች ሰልጠና ጨርሰው ወደ አርሚዎች ቢመደቡም አብዛኛዎቹ ተበትነው ወደየቤታቸው መመለሳቸው አይቀርም የሚለው የታጣቂ ቡድኑ አዛዦች ስጋት እያየለ ባለበት የእነፈትለወርቅ ቡድን አይኑን ጨፍኖ ሀምሌ መጨረሻ ተኩስ ይጀመር የሚል መመሪያ አውርዷል። ጌታቸው አሰፋ በሴንተራል ኮማንድ ውስጥ ገብቶ ጆን መዲድን በዘዴ ሳያካትቱት ስለቀሩ ከእነ ፈትለወርቅና ዶ/ር ደብረፅዮን ጋር ልዩነት ተፈጥሯል።
የህወሓት መሪዎች ለጦርነት እየተዘጋጀን ነው ቢሉም በግዳጅ ወይም በአፈሳ እየመለመሉማሰልጠኛ ካምፕ ያስገቧቸው ወጣቶች የስልጣና ማዕከሉን ጥለው እየኮበለሉ መሆናቸውን የመረጃ ምንጮቻችን ነግረውናል፡፡
በትግራይ ክልል በግዳጅ የተመለመሉ ወጣቶች የስልጠና ካምፖችን ጥለው እየጠፉ እና እያመለጡ መሆኑን የአይን እማኞች፣ የተጎጂ ቤተሰቦች እና የተለያዩ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ሪፖርቶች ያረጋግጣሉ። በግዳጅ ተይዘው ወደ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፖች (ለምሳሌ በምስራቃዊ ዞን በፅራእ ወምበርታ ወረዳ ሓይቅ መስሓል ከተማ እና በአፅቢ ወምበርታ) የተወሰዱ በርካታ ወጣቶች ስልጠናውን ባለመፈለግ ከስልጠና ካምፖች ጠፍተው እየወጡ መሆናቸው ታውቋል።
ወጣቶች እንዳያመልጡ ካምፖቹ በታጣቂዎች በጥብቅ እንደሚጠበቁና ለማምለጥ በሞከሩት ላይ እንዲሁም ልጆቻቸውን ለማስለቀቅ በሞከሩ ወላጆች ላይ ጭምር የሃይል እርምጃ እና ግድያ እንደሚፈጸም የአካባቢው ነዋሪዎች እና የአይን ምስክሮች ለተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
አንዳንዶቹ ወጣቶች በማሰልጠኛ ካምፖች ለአጭር ቀናት ከቆዩ በኋላ ለጠባቂዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ጉቦ በመክፈል አምልጠው በየዘመድ ቤት ይደበቃሉ ወይም ትግራይን ለቅቀው ወደ አዲስ አበባና ወደ ሌሎች ከተሞች ይሄዳሉ።
ከማሰልጠኛ ጠፍተው የወጡትም ሆኑ በአፈሳው ያልተያዙት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች በየቀኑ የመኖሪያ ቦታቸውን በመቀየር፣ ቤታቸውን ጥለው በየሜዳውና በየጫካው በመደበቅ ላይ እንደሚገኙ ሂዩማን ራይትስ ዎች የተሰኘው አለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋም በሪፖርቱ አመልክቷል።














