
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት የአረብ እና የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ በኤክስ የማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሐፍ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር በመሆን በየትኛውም የቀጣናው አገር ላይ እንደማታሴር አስታወቁ።
አማካሪው እንዳሉት አሜሪካ “ከአንድ የቀጣናው አገር በተቃራኒ ከኤርትራ ጋር ድርድር እያደረገች ነው ወይም ምሥጢራዊ ስምምነት ለመድረስ እያሳበች ነው መባሉ ፍጹም ሐሰት ነው” በማለት አስፍረዋል።
ማሳድ ቡሎስ በኤክስ ጽሑፋቸው ላይ አሜሪካ ከኤርትራ ጋር ግንኙነት እያደረገች መሆኑን በተመለከተ ሃሳቡ ከማን እንደተሰነዘረ እና የቀጣናው አገር የተባለው ማን እንደሆነ በስም አልጠቀሱም።
ጨምረውም እንዲህ ያለ ስምምነት አለመኖሩን እና ይህንንም በተመለከተ ንግግር እየተደረገ አለመሆኑን ገልጸው፤ የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ዓላማ “በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ማድረግ ነው” ብለዋል።
ጨምረውም ስምምነቶችን ወይም ሌሎች ክስተቶችን በተመለከተ የሚቀርቡ ሐሰተኛ እና አሳሳች መግለጫዎች፣ ስምን የሚያጠፉ ግምቶች እና መሠረት የሌላቸው ክሶች “በቅን ልቦና የሚደረጉ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶችን በማዛባት ዘላቂ ሰላማን የማስፈን ተስፋን አደጋ ላይ ይጥላሉ” በማለት ወቅሰዋል።
መንግሥታቸው ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ከግብፅ፣ ከኤርትራ እና ከኢትዮጵያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን መከተሉን እንደሚቀጥል የጠቀሱት ቡሎስ፤ የአገራቸው ዋነኛ ትኩረት የቀጣናው ዘላቂ ሰላም መሆኑን አመለክተዋል።
የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከፍተኛ አማካሪ እንዲህ ያለውን ማስተባበያ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሲጽፉ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ይህ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
የአሜሪካው ከፍተኛ ዲፕሎማት ከሁለት ሳምንት በፊት ካይሮ ውስጥ ከኢትዮጵያ አንጻር የጋራ ትብብር ከመሠረቱት ከግብፅ፣ ከኤርትራ እና ከሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ውይይታቸው ፀረ ኢትዮጵያ ዓላማ እንዳልነበረው አሳውቀው ነበር።
አሁንም ባለሥልጣኑ አይጥቀሱት እንጂ አሜሪካ ከቀጣና አገራት አንዷን በተመለከተ ከኤርትራ ጋር ንግግር ወይም ምሥጢራዊ ግንኙነት እያደረገች ነው ሊባል የሚችለው ግንኙነታቸው ተበላሽቶ ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል ከተባለው ከኢትዮጵያ አንጻር ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።













