Image

ባብ ኤል-መንደብ ወሽመጥ (Bab el-Mandeb Strait) በሁቲ ታጣቂዎች መያዙ ወይም በቀይ ባሕር አካባቢ የሚፈጠረው ወታደራዊ አለመረጋጋት በኢትዮጵያ ማክሮ–ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛና ቀጥተኛ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ተመልክቷል።

ኢትዮጵያ ከ90% በላይ የሚሆነውን የወጪና ገቢ ንግድ የምታካሂደው በባብ ኤል-መንደብ አቅራቢያ በሚገኘው በጂቡቲ ወደብ በኩል በመሆኑ፣ በአካባቢው የሚፈጠር ማንኛውም መስተጓጎል የኢኮኖሚ ደህንነቷን አደጋ ላይ ይጥለዋል።

ቀዳሚ የሚሆነው ተፅእኖ የትራንስፖርትና የሎጂስቲክስ ወጪ መናር ነው፡፡ በቀይ ባሕር ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የጭነት መርከቦች ረጅም እና አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ ያስገድዳቸዋል። ለምሳሌ በደቡብ አፍሪካ “ኬፕ ኦፍ ጉድ ሆፕ” ዙሪያ እንዲጓዙ ያደርጋቸዋል፡፡

ይህ ደግሞ የባሕር ላይ ጉዞን በሳምንታት ያራዝማል፣ የኢንሹራንስ ወይም የመድን ዋስትና ክፍያ እና የነዳጅ ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ ይጨምራል። የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የጭነት ድርጅቶች የታሪፍ ጭማሪ እንዲያደርጉ ስለሚያስገድድ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ ዕቃዎች ዋጋ ይንራል። 

ኢትዮጵያ እንደ ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ መድኃኒቶችና ለፋብሪካዎች የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ከውጭ በከፍተኛ ሁኔታ ታስገባለች። የሎጂስቲክስ ወጪ ሲጨምርና ዕቃዎች በወቅቱ ሳይገቡ ሲዘገዩ በሀገር ውስጥ ገበያ ላይ የዕቃዎች እጥረት ይፈጠራል፤ ይህም አሁን ያለውን የዕለት ተዕለት የኑሮ ውድነትና የዋጋ ግሽበትን ይበልጥ ያባብሰዋል።

የኢትዮጵያ ዋና ዋና የውጭ ምንዛሬ መገኛ የሆኑት እንደ ቡና፣ ሰሊጥ እና የቅባት እህሎች ያሉ ምርቶች ለዓለም ገበያ የሚቀርቡት በዚህ መስመር ነው። የመርከቦች መዘግየት ምርቶቹ በወቅቱ ለገዢዎች እንዳይደርሱና ጥራታቸውን እንዲያጡ ያደርጋል። የጭነት ዋጋ መጨመር የኢትዮጵያ ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ ያላቸውን የዋጋ ተወዳዳሪነት ያዳክመዋል።

የየመን ሁቲዎች በባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ የሚገኘውን ቁልፍ ደሴት መቆጣጠራቸው ተዘግቧል። ይህም አውሮፓን ከእስያ ጋር የሚያገናኘውን እና በዓለም ወሳኝ የሆነውን የባሕር ትራንስፖርት መስመር አደጋ ውስጥ ከትቶታል።

ባለሥልጣናት እንደሚሉት የየመን መንግሥት ደጋፊ ኃይሎች አርብ ዕለት ከፔሪም ደሴት ለቅቀው ወጥተዋል። ይህንንም ተከትሎ ለሳምንት ፈጣን ግስጋሴ ሲያደርጉ የነበሩት በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች የየመንን የቀይ ባሕር ዳርቻ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል።

የዓይን እማኞች እንደሚሉት በባብ ኤል መንደብ ባሕር ዳርቻ ታጣቂዎች እየተሰማሩ ሲሆን፣ በዙሪያውም ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እየተንቀሳቀሱ ነው። ሁቲዎች ግስጋሴያቸውን ቀጥለው ወደ አፍሪካ ቀንድ አገራቱ ጂቡቲ እና ኤርትራ ቀርበው የሚገኙትን ሃኒሽ የተባሉትን ደሴቶች ሰኞ ዕለት በቁጥጥራቸው ስር አስገብተው በቀይ ባሕር ላይ ያላቸውን ይዞታ አጠናክረዋል።

በወሽመጡ ላይ የምትገኘው ቁልፍ የሆነችው ፔሪም ደሴት በቁጥጥር ሥር የዋለችው ሁቲዎች የወደብ ከተማዋን ሞካን ከያዙ ከአንድ ቀን በኋላ እንደሆነ ወታደራዊ ምንጮች ገልጸዋል። የሞካ ከተማ ነዋሪዎችም የሁቲ ተዋጊዎች ረቡዕ ዕለት ከመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች ጋር እልህ አስጨራሽ ውጊያ ካደረጉ በኋላ ወደ ከተማዋ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የተቀሰቀሰው ውጊያም በርካታ ነዋሪዎች ቤታቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አድርጓል። አንድ ግለሰብ ውጊያው የተቀሰቀሰው ያለምንም ማስጠንቀቂያ እንደሆነ ለቢቢሲ አረብኛ አገልግሎት የመካከለኛው ምሥራቅ ፕሮግራም ተናግሯል።

“የተጎዱ ሰዎች ያለምንም እርዳታ በመንገድ ላይ ወድቀው በሚታዩበት አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ በርካታ ሰዎች አካባቢያቸውን ለቅቀው እንዲወጡ አስገድዷል” ብሏል።ታጣቂዎቹ ከሳምንት በፊት በሳዑዲ በሚደገፉት የመንግሥት ደጋፊ ኃይሎች ላይ ጥቃት ከከፈቱ አንስቶ በመቶዎች ሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ቢያንስ 46 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች መፈናቀላቸውን አስታውቋል። በግጭቱ ምክንያት በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ ከ1400 ሰዎች በላይ ወሽመጡን አቋርጠው ወደ ጂቡቱ መግባታቸውን የአገሪቱ የኢኮኖሚ ሚኒስትር ኢልያስ ሞሳ ዳዋሌህ ተናግረዋል። ግጭቱ መባባሱም የነዳጅ ዋጋ እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል።

ሁቲዎች በዓለም አቀፍ የባሕር ጉዞ ላይ ስጋት እንደሌለ እና ዒላማ የሚያደርጉት ከሳዑዲ አረቢያ የሚነሱ መርከቦችን ብቻ እንደሆነ ገልጸዋል። ሳዑዲ የሆርሙዝ ወሽመጥ እንዲዘጋ ያደረገው አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ጦርነት ከከፈቱ ወዲህ ነዳጅ ወደ ውጪ የምትልከው በዚህ ወሽመጥ ነው።

ሁቲዎች ዓለም አቀፍ መርከቦችን ዒላማ አናደርግም ቢሉም ቡድኑ ቀደም ብሎ በጋዛ ጦርነት ወቅት ከእስራኤል ጋር ግንኙነት ያላቸው መርከቦችን ብቻ እንደሚያጠቁ ገልጸው፤ ነገር ግን ምንም ግንኙነት የሌላቸው በርካታ መርከቦች ላይ ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ የባሕር ትራስፖርት ድርጅቶች ጥርጣሬ ገብቷቸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም የሁቲ ጦር ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በቴሌግራም ባጋሩት ጽሑፍ ቡድኑ “መጠነ ሰፊ፣ ከፍተኛ ውጤት የሚያስከትል ወታደራዊ ዘመቻ” እንደሚያካሂድ እንደሚያሳውቅ ገልጸዋል።

36 ኪሎ ሜትር ስፋት እና 115 ኪሎሜትር ርዝመት ያለው ባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ፣ በአውሮፓውያኑ 1869 አውሮፓ እና እስያን የሚያገናኝ አጭር የባሕር መስመር የፈጠረው የሱዌዝ ቦይ ሲከፈት በዓለም ንግድ ወሳኝ መስመር ሆኗል።

በመሆኑም የቀይ ባሕር ወሽመጥ አሁን ላይ በዓለማችን እንቅስቃሴ ከሚበዛባቸው መስመሮች አንዱ ሆኗል። አንድ አራተኛ የሚሆነው የዓለም መርከቦች የሚያልፉትም በዚሁ ወሽመጥ ነው።

20 በመቶ የሚሆነው የዓለም ነዳጅ የሚተላለፍበት የሆርሙዝ ወሽመጥ በኢራን ጦርነት ምክንያት ተዘግቷል። የባብ ኤል መንደብ ወሽመጥ መዘጋትም ተጨማሪ 12 በመቶ የሚሆነው የዓለም የነዳጅ አቅርቦት ያስተጓጉላል።

እንግሊዝ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስጠነቀቀች

እንግሊዝ የኤርትራ ዲፕሎማቶችን እንቅስቃሴ እንደምትገድብ አስጠነቀቀች

ሻዕቢያን ከሳህል በረሃ የትጥቅ ትግል ዘመን ጀምሮ ኤርትራን ገንጥሎ መንግስት እስከሚሆን ድረስ በርካታ የአውሮፓ ሀገራት አጋር ሆነው የፋይናስና…

ጥቅም 15, 2026
ኦነግ ለኢሳይያስ ንግግር በመግለጫ ምላሽ ሰጠ

ኦነግ ለኢሳይያስ ንግግር በመግለጫ ምላሽ ሰጠ

የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ትናንት ባወጣው መግለጫ “ህዝባችን ላይ የታወጀና በቀጣናው ደግሞ እየተስተዋሉ ያሉ ችግሮች እየጠነከሩ በመምጣታቸው እንዲሁም…

ጥቅም 14, 2026
የተቋረጠው የትግራይ በረራ በድጋሚ መጀመሩ ምን ያመለክታል?

የተቋረጠው የትግራይ በረራ በድጋሚ መጀመሩ ምን ያመለክታል?

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በጊዜያዊነት ተቋርጦ የነበረውን ወደ መቀሌ ከተማ የሚያደርገውን መደበኛ በረራ እሁድ ከጥቅምት 1 ቀን 2019 ዓ.ም ጀምሮ…

ጥቅም 12, 2026
ኢትዮጵያ ስለተፈጸመባት ወረራ ለተመድ የፀጥታ ም/ቤት አሳወቀች

ኢትዮጵያ ስለተፈጸመባት ወረራ ለተመድ የፀጥታ ም/ቤት አሳወቀች

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዮስ ኢትዮጵያ በኤርትራ ወረራ እንደተፈጸመባት እና ራሷን ከመከላከል ውጪ ሌላ አማራጭ እንደሌላት…

ጥቅም 12, 2026