በዓለማችን የቅርብ ዘመን ታሪክ ከፍተኛ የመበታተን አደጋ የገጠማቸው የባልካን ሀገራት ናቸው፡፡ የባልካን ሀገራትበአውሮፓ ደቡብ ምስራቅ ክፍል በባልካን ልሳነ ምድር ላይ የሚገኙ በርካታ ባህልና ታሪክ ያላቸው ሀገራት ናቸው። ስማቸው የመጣው በቡልጋሪያ ውስጥ ከሚገኘው የባልካን ተራራ ሰንሰለት ነው።
ከእነዚህ ሀገራት መካከል ፖለቲካን የሀብት ምንጭና የዘረኝነት አላማቸውን ማስፈጸሚያ ያደረጉ ፖለቲከኞች እንደ ዩጎዝላቪያ ያሉ ገናና ሀገራት እንዲፈራርሱና ወደ ትናንሽ ደሃ መንግስትነት እንዲቀየሩ ያደረጉባቸው ናቸው፡፡
ታጣቂ ኃይሎች የፈጠሩት ጥምረት ኢትዮጵያን ለባልካናይዜሽን (የመበታተን አደጋ) ልትጋለጥ የምትችልበት ዕድል በፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ ሰፊ ክርክር የሚደረግበት ጉዳይ ሆኗል። አንዳንድ የፖለቲካ ምሁራን ይሄንን እንደ ትልቅ ስጋት ሲያዩት፣ ሌሎች ደግሞ ሀገሪቱን ከመበታተን የሚያድኑ ጠንካራ ማህበራዊና ታሪካዊ መስተጋብሮች መኖራቸውን ይገልጻሉ።
የባልካናይዜሽን ስጋትን ሊያሳድጉ ይችላሉ ተብለው ከፍተኛ ግምት ከተሰጣቸው ጉዳዮች አንዱና ዋናው የቡድኖቹ በብሔርና በዘር ማንነት ላይ የተመሰረተው አደረጃጀት ነው፡፡ አብዛኞቹ ታጣቂዎች የተዋቀሩት በብሔር ማንነት ላይ በመሆኑ ጥምረቱ ሲፈርስ ወደየብሔራቸው የመሸሽ ዕድላቸው ከፍተኛ ነው።
በቡድኖቹ መካከል ቀደም ሲል የነበረው በብሔር ጥላቻ ምክንያት የጎሪጥ መተያየትና የጋራ ስምምነት እንዲሁም በክልሎች መካከል ያሉ የይዞታ ጥያቄዎች ጥምረቱ ሲፈርስ ወደ ለየለት የእርስ በርስ ግጭት ሊያመሩ ይችላሉ።
ገና ከጅምሩ ጥምረቱ መመስረቱን ተከትሎ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ልዩ ልዩ ዓላማ ያላቸው አደረጃጀቶች በተለይ በማኅበራዊ መገናኛ ዐውታሮች አወንታዊ ምላሽም፣ ብርቱ ትችትም በመሰንዘር ላይ ናቸው።
የወልቃይት ጠገዴ አማራ የማንነትና የወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ጉዳዩን በአሉታ ከተመለከቱ ተቋማት አንዱ ሲሆን “በሕዝባችን ማንነት፣ ህልውና እና ወሰን ላይ የሚደረጉ ሕገ-ወጥ የጀርባ ሴራዎችንና ስምምነቶችን የአማራም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥንቃቄና በንቃት ሊመለከት ይገባል” በማለት ትብብሩን አጥብቆ ነቅፏል።
ከጥምረቱ መስራቾች አንዱ ነው የተባለው የኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) ከዚህ በፊት ለሁለት መከፈሉ ተዘግቧል። አንደኛው እና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው አንጃ በጥምረቱ ተሳትፎ እንደሌለው ጠቅሶ በድርጅቱ የቀድሞው ሊቀመንበር የሚመራ ያለው ቡድን የሚሰራጨው መግለጫ አቋሙ እንዳልሆነ ገልጿል።
በድርጅቱ የቀድሞው ሊቀመንበር አብዱራሕማን ሼክ ማህዲ የሚመራና በውጭ ሀገር የሚገኘው የኦብነግ አንጃ ግን የዚህ ጥምረት መስራች መሆኑ ታውቋል።
ሰባት ታጣቂና የፖለቲካ ኃይላትን ያቀፈ ትብብር መመስረቱ መነገሩን ተከትሎ ግለሰቦች፣ ተቋማትና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች አወንታዊም አሉታዊም አስተያየቶችን እየሰነዘሩ ነው። የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የትግራይ ቴሌቪዥንን ከትናንት ጀምሮ ማገዱን መግለፁ፣ የዚህን ጥምረት ይፋ መደረግ ተከትሎ የተስተዋለ ጉልህ ርምጃ ሆኗል።
የአፍሪካ ሕብረትና ሌሎች ቀጣናዊ ተቋማት በጉዳዩ ላይ እስካሁን ያሉት ነገር የለም። የመንግሥታቱ ድርጅት ግን ኢትዮጵያ ውስጥ “የታጠቁ ቡድኖች ጥምረት መፈጠርን እንዲሁም የቀጠለ” ያለውን “የጸጥታ መደፍረስ እና የድሮን ጥቃት በተመለከተ ከፍተኛ ሥጋት” እንዳለው ገልጿል።
“ትብብር ለሕልውና” የተባለው ኃይል በስድስት ክልሎች ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ራሳቸውን “ሕዝባዊ ኃይሎች” ብለው የሰየሙ ሰባት የትጥቅ እና የፖለቲካ ኃይሎች የመሠረቱት አካል መሆኑ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በትግራይ ቴሌቪዥን ላይ “ላልተወሰነ ጊዜ እገዳ መጣሉን”፣ ማንኛውም መገናኛ ዐውታር ጣቢያውን እንደ መረጃ ምንጭ እንዳይጠቀም ማሳሰቡ እና ያንን በሚተላለፉት ላይ ሕጋዊ እና አስተዳደራዊ ርምጃ እንደሚወስድ ማስጠንቀቁ የጥምረት ዜናውን ተከትሎ የተሰማ ጉልህ ውሳኔ ሆኗል።
የአብሮነት ኢትዮዽያ የተባለው የፖለቲካ ኃይል በአንፃሩ ለዚህ ትብብር በጎ ምላሽ ሰጥቷል። ስምምነት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ነው ያለው ጦርነት በአጭሩ ተቋጭቶ ጦርነት እንዲቆምና ሰላም እንዲሰፍን፣ በዜጐች ላይ ይደርሳል ያለውን ጉዳት እንደሚቀንስ በከፍተኛ መጠን እንዲቀንስ የሚያደርግ፤ ሁሉን-አቀፍ የሽግግር ሂደት እንዲፈጠር እንደሚያግዝ ጠቅሶ ይህን ስምምነት ሕዝቡ በሙሉ ልብ ሊደግፈው እንደሚገባ አቋሙን ይፋ አድርጓል።
በጉዳዩ ላይ ሰፊ የዘገባ ሽፋን ከሰጡ ዓለም አቀፍ መገናኛ ዐውታሮች አንዱ የሆነው ሮይተርስ የዜና አግልግሎት ትናንት ባወጣው ዘገባ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ቃል አቀባይ ቢለኔ ስዩም የጥምረቱ አባላት የኢትዮጵያ ጎረቤትና ታሪካዊ ተቀናቃኝ ከሆነችው ኤርትራ በሚደረግላቸው የገንዘብ ድጋፍ ለተወሰነ ጊዜ ሲተባበሩ እንደቆዩ “በቅርቡ የተሰጠው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ደጋግሞ ሲናገርበት የቆየውን ጉዳይ የሚያረጋግጥ ነው” ሲሉ ትናንት በጽሑፍ መልዕክት እንደገለፁለት ጽፏል።
የኢትዮጵያን የፖለቲካ ኹኔታ በቅርበት የሚከታተሉ አንድ ተንታኝ በሁሉም ወገን “የድርድር ሀሳብ እና ፈቃድ ካለ” ታጣቂዎቹ ወደ አንድ መምጣታቸው “በከፊል በጎ ነገር ነው”፣ ሆኖም ይህ ኃይል ግቡ ቢሳካ “በድኅረ መንግሥት ማስወገድ ወቅት” ኢትዮጵያ “ከባድ ፈተና ሊገጥማት እንደሚችል” ያላቸውን ምልከታ ትናንት አጋርተዋል።
“በየትኛውም መንገድ – በድርድር፣ በሰላም ነገሮችን መስመር ማስያዝ ከተቻለ እንደ ሀገርም እንደ ቀጣናም እሰይ የሚያሰኝ ውጤትን ይዞ ይመጣል። በአንድ በኩል ደግሞ ያለመሳካትም ዕድል ስላለው የባልካናይዜሽን ችግር ይገጥመን ይሆን ወይ” የሚል ሥጋት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ትናንት በሰጡት መግለጫ “በኢትዮጵያ እየተባባሰ የመጣውን የጸጥታ ኹኔታ እና በቅርቡ የታዩ ክስተቶችን፣ ማለትም የአዳዲስ የታጠቁ ቡድኖች ጥምረት መፈጠርን የቀጠለውን የጸጥታ መደፍረስ እና የድሮን ጥቃቶች በተመለከተ ከፍተኛ ሥጋት አለን።” ብለዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት “ውጥረት በከፍተኛ ደረጃ ባየለበት በዚህ ወቅት፣ ኹኔታውን የበለጠ ሊያባብሱ ከሚችሉ ድርጊቶች ወይም ንግግሮች እንዲቆጠቡ” እና “ለውይይት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያድሱ” ጠይቀዋል።
“ወታደራዊ ርምጃ የፖለቲካ ልዩነቶችን አይፈታም” ያሉት የአንቶኒዮ ጉቴሬዥ ቃል ዐቀባይ “መሰረታዊ ቅሬታዎችንም አይፈታም።” ብለዋል። የመንግሥታቱ ድርጅት የፕሪቶሪያው ዘላቂ ግጭት የማቆም ስምምነት እንዲከበር በአፍሪካ ሕብረት የሚመሩ ጥረቶችን መደገፉን እንደሚቀጥልም ቃል ዐቀባዩ ገልፀዋል።














