ከህወሓት እና ከፋኖ ጋር በመሆን “ትብብር ለኅልውና” የሚል ጥምረት የመሠረተው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት “ኢምፓየሯን ኢትዮጵያንና ያለው ሥርዓተ መንግስት መፍረስ አለበት” የሚለውን አቋሙን እንዳልተወ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑት አቶ ጂሬኛ ጉደታ አስታወቁ።
ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ተለይቶ የትጥቅ እንቅስቃሴ የሚያደርገው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (ኦነሠ) አዛዥ አማካሪ ከቢቢሲ አፋን ኦሮሞ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ስለ ኢትዮጵያ ቀጣይነት እና በቅርቡ ስለ ተመሠረተው እና አባል ስለሆነበት የታጣቂ ቡድኖች ጥምረት ተናግረዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አዛዥ አማካሪ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ ከህወሓት እንዲሁም ከፋኖ ጋር ስለመሥራት እና ስለመተባበር ሲጠየቁ ቡድናቸው “የጥንቱ አቋማችን ላይ ነን፤ የኢምፓየሩ ሥርዓት መፍረስ አለበት የሚለውን አቋማችንን አልተውንም” ሲሉ መልሰዋል።
በኦሮሚያ ክልል በተለይም በምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ዞኖች ኦነሠን ጨምሮ የተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች በሚፈጽሙት ጥቃት የተነሳ የአካባቢው ሕዝብ ላለፉት አምስት ዓመታት በሰላም እጦት እየተሰቃየ ነው።
ነዋሪዎቹ በተለያየ ጊዜ ለቢቢሲ “በሦስት ጥይት እየተመታን ነው” ሲሉ ከመንግሥት ወታደሮች እንዲሁም በፋኖ ስም ከሚንቀሳቀሱ እና ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አማፂያን ላይ ቅሬታቸውን ያሰማሉ።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከፋኖ ጋር በመሆን “ትብብር ለኅልውና” የሚል ጥምረት የመሠረተው በዚህ ሁሉ ቅሬታ መካከል ነው።
ቢቢሲ አፋን ኦሮሞ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ዋና አዛዥ አማካሪ የሆኑትን አቶ ጂሬኛ ጉደታን ከፋኖ ጋር ባላቸው ግንኙነት ምን ያህል እንደሚተማመኑ ሲጠይቃቸው “በፖለቲካ ውስጥ መተማመን የሚባል ነገር የለም፤ ያለው የሕዝብ ጥቅምን ማስጠበቅ ብቻ ነው” ብለዋል።
አቶ ጂሬኛ አክለውም “አሁን የሚነደውን ትልቅ እሳት ትተን፣ ትንንሽ እሳት ያላቸውን አሳንሰን አናይም” ሲሉም በክልሉ እንደሚንቀሳቀስ ከተናገረው ፋኖ ጋር ወደፊት “በግልጽ እንደሚነጋገሩ” አስረድተዋል።
ድርጅታቸው የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት የኦሮሞ ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ቡድን መሆኑንም ጨምረው ተናግረዋል። የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ከ50 ዓመት በፊት ሲመሠረት ጀምሮ ሕዝቡ ነጻ ሆኖ ራሱን እንዲያስተዳድር ማድረግ ከዓላማዎቹ መካከል አንዱ ነበር። ኦነግ የትጥቅ እንቅስቃሴ የጀመረው የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን ላይ ሳለ ነው።
ኦነግ የትጥቅ ትግል ሲያካሂድ ቆይቶ በደርግ መውደቂያ አቅራቢያ ከኤርትራው ህግሓኤ እና ከህወሓት ጋር ግንባር በመፍጠር የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም እና አሁን ያለው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት በማዘጋጀት ጉልህ ሚና ነበረው።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከኦሮሞ ነፃነት ግንባር ተገንጥሎ የወጣ ታጣቂ ቡድን ሲሆን፣ በተለያዩ የኦሮሚያ ክፍሎች ውስጥ ይንቀሳቀሳል። የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከዚህ ቀደም ኦነግን ወደ ጫካ ዳግም እንዲመለስ ካደረገው ህወሓት እንዲሁም በኦሮሚያ ታጣቂዎች እንዳሉት ከገለጸው ፋኖ ጋር የሚሠራው እንዴትት እንደሆነ አቶ ጂሬኛ ተጠይቀዋል።
አማካሪው ሲመልሱም በትብብር ለኅልውና ውስጥ የታቀፉት ታጣቂዎች በፖለቲካ አስተሳሰብ አንድ አለመሆናቸውን ተናግረዋል። “እኛ ያደረግነው ትብብር የአሠራር ሂደት ብቻ ነው እንጂ አንድ አልሆንም።… በመጀመሪያ፣ አንድ ነን ብሎ መናገር ትልቅ ስህተት ነው። እኛ የተነጋገርነው በውይይት ሂደት እና ሕዝባችን የራሱን ሚና በነፃነት በሚወስንበት ሂደት ላይ ነው” ብለዋል።
አቶ ጂሬኛ አክለውም “ትብብር ለኅልውናን” ለመመሥረት ያነጋገሯቸው አካላት ወደ ኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መምጣታቸውን ገልጸው፣ “እነርሱ ናቸው ወደ እኛ የመጡት፣ እኛ አይደለንም ወደ እነርሱ የሄድነው” ብለዋል።
አቶ ጂሬኛ ይህንን ሲያብራሩም የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ኢትዮጵያ “ለማፍረስ” ያላውን አቋም አለመተዉን ተናግረዋል። “እኛ ያለንበት ቦታ ያው ነው። የኢምፓየሩ ሥርዓት መፍረስ አለበት የሚለው አቋማችንን አልተውንም። እነርሱ መጥተው ያንን ሥርዓት፣ ያንን ኢምፓየር እንደሚያፈርሱት ሲናገሩ እንደግፋቸዋለን። ከስትራቴጂያችን አላፈነገጥንም።”
አቶ ጂሬኛ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊትን ወደ “ትብብር ለኅልውና” እንዲቀላቀል ግብዣ ያቀረበለት ማን እንደሆነ አልተናገሩም። ነገር ግን “የኢምፓየሩን ሥርዓት እናፍርስ? ብለው ሲጠይቁን ‘አይሆንም’ ካልክ፣ ሞኝ ነህ ማለት ብለዋል። ቡድኑ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ድርደር ባደረገበት ወቅት አቋሙ ተመሳሳይ እንደነበር አቶ ጂሬኛ አስታውሰዋል።
“እኛ ያደረግነው የሁሉም ሕዝቦች መብት የሚከበርበትን አሠራር መዘርጋት ነው። ይህ ስህተት ሊሆን አይችልም። ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ስንደራደርም ያደረግነው ይህንኑ ነው።” ቢቢሲ አቶ ጂሬኛን ፋኖ ካለው አቋም ጋር እንዴት ተስማምተው እንደሚሠሩ ሲጠይቃቸው “እኛ የተባበርንበት ምክንያት ሕዝባችንን የሚገድል አካል አለ፤ የደኅንነት ስጋትም አለ።. . . ይህ ደግሞ የሚያመለክተው ዛሬ ያለውን ሁኔታ ነው፤ ማለትም የመንግሥት ሥልጣን በእጁ ያለውን አካል ነው” ብለዋል።
በሥልጣን ላይ ያለው አካል ፋኖ እና ህወሓት አለመሆናቸውን በመግለጽም “ሕዝቡ የራሱን ዕድል በራሱ የሚወስንበትን ሥርዓት ካልተቃወሙ” በስተቀር ችግር እንደማይኖርባቸውም አስረድተዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት በ’ትብብር ለኅልውና” ውስጥ በመሳተፉ “የሚያጣው ነገር የለም። አመራሩ በትግል ሜዳ ላይ ነው ያለው። እንደ ቀድሞው ወጥመድ ውስጥ እንገባ ይሆን? ብለን መጨነቅ አያስፈልገንም። ሠራዊቱ ታጥቆ ነው ያለው፤ ትጥቁን አልፈታም፤ ዓላማውም በልቡ ውስጥ ነው። ታዲያ በዚህ ጉዳይ ምን የሚያስጨንቀው ነገር አለ?” ሲሉ አስረድተዋል።
በክልሉ በፋኖ ታጣቂዎች ስለሚፈጸሙ የተለያዩ ጥቃቶች የተጠየቁት አቶ ጂሬኛ “በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚፈጸሙ ወንጀልን ማንም ይፈጽመው ማንም ወንጀል ነው፤ የአገር ጠላትነት ነው” ካሉ በኋላ ታጣቂዎች ያላቸው አቅም ግን የፌደራል መንግሥቱ ከታጠቀው ጦር መሣሪያ እና ድሮን ጋር ማወዳደር እንደማይቻል ይናገራሉ።
አቶ ጂሬኛ የቡድናቸው ርዕዮተ ዓለም ከሌሎቹ በ”ትብብር ለኅልውና” ውስጥ ከተካተቱት ጋር እንደማይገናኝ ሲጠየቁም “በመጀመሪያ፣ ትልቅ አደጋ አለ፤ ትልቁ አደጋም ‘ፒፒ’ (ብልጽግና ፓርቲ) ነው። ከዚህ የበለጠ አደጋ አለ ብለን አናምንም። ስለዚህ፣ ይህንን አደጋ እናስወግዳለን። ከዚያም፣ ያንን ኃላፊነት ስንወስድ፣ ጊዜያዊው መንግሥት ተቋቁሞ ሥራውን ይጀምራል” ብለዋል።
የሽግግር መንግሥት ከተመሠረተ በኋላ የማያስማሙ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ቢኖሩ ለሕዝበ ውሳኔ እንደሚቀርብም ተናግረዋል። ነገር ግን በዚህ ሂደት ውስጥ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ከአቋሙ እንዳይዛነፍ የሚያደርግ አመራር መኖሩን ጨምረው ተናግረዋል።
“አሁን ያለው ትውልድ እንዲህ ዓይነት ኪሳራ እንዳይደርስበት የሚጠብቅ አመራር ቦታውን ይዞ ነው ያለው። ሠራዊቱ በእርሱ ቁጥጥር ስር ነው፤ እንደታጠቀ ነው፤ ዓላማውም በአእምሮው እና በልቡ ውስጥ ነው” ብለዋል።
የትብብር ለኅልውና አባላት የማይስማሙባቸው ጉዳዮችን በሕዝበ ውሳኔ እንደሚፈቱም ተናግረው “በማንስማማባቸው ጉዳዮች ላይ ያለንን ልዩነት ለሕዝብ እናቀርባለን፤ ሕዝቡ ውሳኔ ይሰጣል፤ ከዚያም ሕዝቡ የወሰነውን እንቀበላለን” ብለዋል። የጥምረቱ አባል ቡድኖች ባጋሩት መገለጫ ላይ በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በማስወገድ “በሽግግር ቻርተር የሚመራ አካታች የሽግግር መንግሥት” ለመመሥረት ዓላማ አላቸው።
የኢፌዴሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማወክ እና ለማዳከም ሲሉ አዲስ የተመሰረተውን የታጠቁ እና የፖለቲካ ቡድኖች ስብስብ ከጀርባ ሆነው እየደገፉ ይገኛሉ ሲሉ ከሰሱ፤ ጥረቱንም ከውጭ በሚደረግ ድጋፍ ሲካሄድ የቆየ ፕሮጀክት አዲስ መልክ ይዞ መምጣት ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ለመከላከያ ሠራዊት የመገናኛ ብዙኃን በሰጡት መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ወቅታዊ የደህንነት ፈተናዎች አገሪቷን በቀጥታ ወታደራዊ ወረራ የማጥቃት አቅም የሌላቸው «ታሪካዊ» እና «ወቅታዊ» ጠላቶች የምንላቸው አካላት የሰፊው ስልታቸው አካል እንደሆነ ተናግረዋል።
«ስልታቸውን ቀይረዋል። ስልታቸውን ቀይረው ውስጣችንን እርስ በእርሳችን እንድንባላ፣ እንድንጋደል፣ ሰላም እንድናጣ፣ እንዳንለማ፣ የተፈጥሮ ሀብታችንን እንዳንጠቀም ለማድረግ ገንዘብ ኢንቨስት አድርገው፣ ደህነኛ አሰማርተው ውስጣችንን የመበጥበጥ ነገር ነው ያለው» ብለዋል።
ፊልድ ማርሻል ይህንን የተናገሩት፣ የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ፣ ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ፣ የኦጋዴን ሕዝብ ነጻነት ግንባር፣ የአፋር ብሔራዊ አንድነት አብዮታዊ ግንባር፣ የቤኒሻንጉል ሕዝቦች ነጻነት ንቅናቄ እና የጉሙዝ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን ያካተተውና «የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ኃይሎች ትብብር ለህልውና» (በአጭሩ «ትብብር ለህልውና») የተሰኘው ትብብር መመስረቱን ከገለጸ ከጥቂት ቀናት በኋላ ነው።














