ታህሳስ 20 ቀን 2014 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 የተመሰረተው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በመጪው ሐምሌ ሊካሄድ ቀን በተቆረጠለት አገር አቀፍ ጉባኤ ለውይይት የሚቀርቡ ስምንት ዋነኛ አጀንዳዎችን ይፋ አደረገ።
ኮሚሽኑ የተቋቋመበት አላማ በዘመናት ውስጥ ሲከማቹ ለቆዩ አገራዊ የፖለቲካ እና የሀሳብ ልዩነቶች አካታች፣ አሳታፊ እና ገለልተኛ በሆነ መንገድ ሰፊ የህዝብ ውይይት በማካሄድ ዘላቂ መግባባት ለመፍጠር ነው።
የኮሚሽኑ የሥራ ዘመን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውሳኔ ሁለት ጊዜ እንዲራዘም የተደረገ ሲሆን ይኸውም በየካቲት 2017 እና በየካቲት 2018 ዓ.ም በአንድ ዓመት እና በስምንት ወራት እንዲራዘምለት ተደርጎ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ኮሚሽኑ በተራዘመለት በዚህ የስራ ጊዜ ውስጥ ሰፊ አገራዊ አጀንዳዎችን በመለየት ዋናውን የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ መጀመሩ ይታወቃል።
በትናንትናው ዕለት ኮሚሽኑ ይፋ ካደረጋቸው የምክክር አጀንዳዎች መካከል “የመንግሥት አደረጃጀት ሥርዓት ዓይነት” እና በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 የተደነገገው “የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት” ጉዳዮች ተካትተዋል።
ኮሚሽኑ በስምንተኛነት በያዘው “የሰላም ግንባታ” አጀንዳነት ሥር ደግሞ “ግጭቶች እና መሣሪያ ያነሱ አካላት” እንዲሁም “የተኩስ አቁም እና የሰላም ስምምነቶች” ጉዳይ ምክክር እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።
አዲስ አበባ ከተማ “ከኦሮሚያ ክልል ጋር ያለው ግንኙነት” እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ “የወደፊት አስተደዳር ሁኔታ” የሚሉትም የምክክሩ አጀንዳዎች ሆነዋል። የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ይህንን ያስታወቀው ረቡዕ ሰኔ 17/2018 ዓ.ም ምሽት ባካሄደው የአጀንዳዎች ይፋ ማድረጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ነው።
ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደገለጹት “ላለፉት አራት ዓመታት” በአገር አቀፍ ደረጃ በተካሄዱ መደረኮች እና በሌሎች መንገዶች ከተሰበሰቡት አጀንዳዎች መካከል “ስምንት አገራዊ አጀንዳዎች” ተለይተዋል።
ስምንቱ አጀንዳዎች “ዋና ዋና ጭብጦች” እንደሆኑ ያስረዱት ዋና ኮሚሽነሩ፤ እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች በሙሉም በሥራቸው “ንዑስ ጭብጥ” እንደያዙ ተናግረዋል። ኮሚሽነሩ በቀዳሚነት ይፋ ያደረጉት “የአገር ግንባታ” የሚለውን አጀንዳ ነው። በዚህ አጀንዳ ስር ከተካተቱ ንዑስ ጉዳዮች መካከል “የማንነት እና የአገር ባለቤትነት” እንዲሁም “የጋራ ሀገራዊ ማንነትና እሴቶች” ተጠቃሽ ናቸው።
“የመንግሥት አደረጃጀት እና ቅርፅ” የሚል ርዕስ የተሰጠው ሁለተኛው አጀንዳ፤ ኢትዮጵያን “የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት” የሚዳስሱ ጉዳዮች ተካትተውበታል።
በዚህ ዋና አጀንዳ ስር “የመንግሥት አደረጃጀት፣ አስተዳደር ሥርዓት ዓይነት” እና “የአገሪቱ ምርጫ ሥርዓት” ተጠቅሰዋል። “የፌደራል መንግሥት እና የክልል መንግሥታት መሪዎች የሥልጣን ዘመን” የሚለውም በዚህ ዋና አጀንዳ ሥር ምክክር እንደሚደረግበት ዋና ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል።
ይህ ሁለተኛ ዋና አጀንዳ የራስን ዕድል በራስ ከመወሰን ጋር የተያያዙ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችንም ይዟል። ለብሔር ብሔረሰቦች እስከ መገንጠል ድረስ መብት የሰጠው የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 ንዑስ አንቀጽ 1 ጉዳይ የተካተተው በዚህ ዋና አጀንዳ ሥር ነው።
“የአዳዲስ ክልሎች አመሠራረት” እና “የፌደራልና የክልል መንግሥታት ግንኙነት” የሚሉትም ተነስተዋል። “የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሥርዓትን” የሚመለከትም ንዑስ አጀንዳም አብሮ ተጠቅሷል።
ፕሮፌሰር መስፍን በሦስተኛ አጀንዳነት ይፋ ያደረጉት የፌደራል ከተሞች የሆኑት አዲስ አበባ እና ድሬዳዋን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ነው። በኮሚሽኑ የአጀንዳ ዝርዝር መሠረት የሁለቱ ከተሞች “ሕጋዊ አቋም” ለምክክር ይቀርባል።
አዲስ አበባ ከተማ ከኦሮሚያ እንዲሁም ድሬዳዋ ከኦሮሚያ እና ከሶማሌ ክልሎች ጋር የሚኖራቸው ግንኙነትም እንዲሁ ተካትቷል። አዲስ አበባን በተመለከተ ከተነሱት ንዑስ አጀንዳዎች መካከል “የፌደራል ዋና ከተማ ጉዳይ”፣ የከተማዋ “ፖሊስ እና ፍርድ ቤት ጉዳይ” እንዲሁም “ወሰን እና የቦታዎች ስያሜዎች” ይጠቀሳሉ።
ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ በፌዴራል መንግሥት እንዲሁም በፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ የሚኖራት ውክልና ምክክር ይደረግበታል። አራተኛው አጀንዳ “የሃይማኖት ጉዳዮች” የሚነሱበት ሲሆን፣ በሥሩም “የሴኩላሪዝም” ጉዳይ እንዲሁም “የሃይማኖት ነፃነት እና ገደቦቹ” ተጠቅሰዋል።
የሃይማኖቶች “ታሪካዊ መገፋት እና ልዩ ተጠቃሚነት” የሚሉ ጉዳዮችን የሚያነሳው ይህ ዋና አጀንዳ፤ “ሃይማኖቶች መካከል ያሉ ውጥረቶች እና መፍትሄዎቻቸው” የሚል ንዑስ ርዕስንም አካትቷል። የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአምስተኛነት የያዘው “የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነት እና ሰብዓዊ መብቶች” የሚል አጀንዳን ነው። “በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሰዎች መብቶች” እንዲሁም “የጣምራ ዜግነት መብት ዕውቅና” ከዚህ ዋና አጀንዳ ዝርዝሮች መካከል ናቸው።
“ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ” በሚል የተጠቀሰው ስድስተኛው ርዕስ፤ ሴቶችን፣ የአርሶ እና አርብቶ አደሮችን እንዲሁም ሠራተኞችን የተመለከቱ ጉዳዮች ይነሱበታል። ሰባተኛው አጀንዳ ደግሞ “ከሙስና እና መልካም አስተዳደር” ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን ይዳስሳል።
ዋና ኮሚሽነት ፕሮፌሰር መስፍን በመጨረሻ የጠቀሱት ዋና አጀንዳ “ሰላም ግንባታ” የሚል ነው። ይህ አጀንዳ “የግጭት መንስኤዎች እና አፈታት መንገዶች” የሚል ንዑስ ርዕስ የተካተተበት ሲሆን “መሳሪያ ያነሱ አካላትን” የሚመለከቱ ጉዳዮችንም ይዳስሳል። “የተኩስ አቁም እና የሰላም ስምምነቶች” እንዲሁም “የሽግግር ፍትሕ” ምክክር የሚደረግበት በዚህ ዋና አጀንዳ ሥር ነው።
ፕሮፌሰር መስፍን እንደገለጹት በመጪው ሐምሌ 8/2018 ዓ.ም ለሚጀመረው አገር አቀፍ ጉባኤ የተያዙት እነዚህ ስምንት ዋነኛ አጀንዳዎች የተመረጡት “አገራዊ ፋይዳ ያላቸው በመሆናቸው” ነው። በስራቸው የተካተቱት ንዑስ አጀንዳዎችም ለጉባኤው ተሳታፊዎች “እንደ መነሻ ጥያቄዎች ሆነው” እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል።














