የሊቢያው ኦላ ኢነርጂ ግሩፕ (OLA Energy Group) የፈረንሳዩን የኃይል ኩባንያ ቶታልኢነርጂስ (TotalEnergies) በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የነዳጅ ማከፋፈያ እና ተያያዥ ንብረቶች ለመግዛት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርሟል። ይህ የግዢ ስምምነት የሊቢያውን ኩባንያ በኢትዮጵያ የነዳጅ ገበያ ውስጥ ትልቁ የውጭ ሀገር ኩባንያ ያደርገዋል።
ዘ ሊቢያ ኦብሰርቨር እንደዘገበው፥ በፓሪስ ከተማ በተከናወነው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ የሊቢያው የነዳጅ እና ጋዝ ሚኒስትር ኻሊፋ አብዱልሳዲቅ፣ የቶታል ኢነርጂስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፓትሪክ ፑያኔ እንዲሁም የኦላ ኢነርጂ ሊቀመንበር አቡዘድ ሱዋሌም ተገኝተዋል።
ስምምነቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ ወደ 120 ገደማ የሚሆኑ የነዳጅ ማደያ ጣቢያዎችን፣ 13 ሺህ ሜትር ኩብ የመያዝ አቅም ያለውን የነዳጅ ማከማቻ ተርሚናል እንዲሁም ተያያዥ የሥራ እና የንግድ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ የሚያጠቃልል ነው።
ይህ የኩባንያ ግዢ ኦላ ኢነርጂ በኢትዮጵያ የነዳጅ ማከፋፈያ ዘርፍ ውስጥ ትልቁ የውጭ ሀገር ኩባንያ እንዲሆን የሚያስችለው ቢሆንም፥ ለግዢው የተከፈለው የገንዘብ መጠን ግን በይፋ አልተገለጠም።
በትሪፖሊ የሚገኘው የሊቢያ ብሔራዊ አንድነት መንግሥት ይህንን ግዢ የሊቢያን ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖ በአፍሪካ ገበያዎች ላይ ለማስፋፋት እና በሊቢያ ብሔራዊ ኩባንያዎች የሚደረጉ የውጭ ሀገር ኢንቨስትመንቶችን ለማጠናከር ከሚደረጉ ጥረቶች አካል አድርጎ መግለጹ በዘገባው ተመላክቷል። ስምምነቱ ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ አጋርነትን ለመደገፍ እና በአህጉሪቱ አዳዲስ የትብብር እና የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑም ተጠቅሷል።
ይህ ስምምነት ቶታልኢነርጂስ በኢትዮጵያ ውስጥ ለብዙ አሥርተ ዓመታት ሲያካሂድ የቆየውን የነዳጅ ችርቻሮ ንግድ ሙሉ በሙሉ አቁሞ ከሀገሪቱ ገበያ እንዲወጣ የሚያደርገው ሲሆን፥ በአንጻሩ ደግሞ የኦላ ኢነርጂን አሻራ በምሥራቅ አፍሪካ ትልቁ የነዳጅ ገበያ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሰፋው ይሆናል።














