ህወሓት ከፌዴራል መንግሥት ጋር ለመደራደር ፍላጎት እንዳለው በመግለጽ፣ ድርድሩ በአዲስ አበባ ሳይሆን በሌላ የሶስተኛ ወገን ሀገር እንዲካሄድ እንደሚፈልግ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/ሄር ወይም ሞንጆሪኖ ትላንት ለክልሉ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
” አስገዳጅ አፈሳ አለ” በሚል የሚሰራጨው መረጃ የተጋነነ እና ሽብር ለመፍጠር የተሰራጨ ነው ሲሉ አጣጥለዋል። ነዋሪዎች፣ የተለያዩ ተቋማት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በክልሉ አስገዳጅ ወታደራዊ አፈሳ እየተካሄደ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል ወ/ሮ ፈትለወርቅ ” የኢትዮጵያ መንግሥት ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ትግራይ ሰራዊቱን በማሰማራት ለጦርነት እየተዘጋጀ ነው ” የሚል ክስም አሰምተዋል። አንዳንድ የቀድሞ የትግል አጋሮቻቸውን ደግሞ ” ብሔራዊ ከሃዲያን ” በማለት ተናግረዋቸው ” የትግራይን ትግል ለማዳከም እየሠሩ ነው ” ሲሉ ወቅሰዋል።
አሜሪካ “Hardliners” በሚል የጣለችው የቪዛ እገዳን በተመለከተም ” በግለሰቦች ላይ ሳይሆን በድርጅቱ አቋምና መርህ ላይ ያነጣጠረ ነው ” ብለዋል።
አሜሪካ በህወሓት አመራሮች እና ቤተሰቦቻቸው ላይ የቪዛ እገዳ መጣሏ ይታወቃል። የአውሮፓ ህብረትም ህወሓትን በመኮነን መግለጫ ያወጣ ሲሆን ወ/ሮ ፈትለወርቅ ይህን መግለጫዎችና የአሜሪካንን እገዳ ” ሚዛናዊ አይደሉም ” ሲሉ ተችተዋል።
“የፕሪቶሪያ ስምምነትን የጣሰው የኢትዮጵያ መንግሥት ነው” ሲሉ በመክሰስ፣ “እኛ በትግራይ ሕዝብ ጥቅም ላይ አንደራደርም” ሲሉ ተደምጠዋል። “በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ የትግራይ ተወላጅ ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ሁሉም ወገኖች እንዲተባበሩ” የሚል ጥሪም አቅርበዋል።
በሞንጆሪኖ የቀረበው መግለጫ ህወሓት ለሠላማዊ ውይይት ዝግጁ መሆኑን የሚያሳይ ቢመስል መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ከዚህ የራቀ ነገርመኖሩን ያመለክታል፡፡ በተለያዩ ገለልተኛ አካላት እንደተረጋገጠው የፍልሚያ ሜዳውን ከሰሜን ኢትዮጵያ ወደ ምዕራብ ቀይሮ ሱዳን ውስጥ ያስቀመጠውን አርሚ ሰባ በቤንሻንጉል በኩል አንቀሳቅሶ ጦርነት ለመጀመር እየተዘጋጀ ስለመሆኑ ተረጋግጧል፡፡
“ህወሓት ከጦርነት ውጭ ከባህር የወጣ አሳ ይሆናል” በሚል እንደ ቀልድ የሚነገረው አባባል ትክክለኛ የድርጅቱን ባህሪ የሚገልፅ መሆኑን አመራሮቹ ሰሞኑን የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በግልፅ ያመለክታል፡፡
በፌደራል መንግሥቱ እና በህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) መካከል ያለው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈጻፀም መጓተት እና በቅርቡ የተፈጠሩ የፖለቲካ ውጥረቶች በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም የጦርነት ስጋት እንዲያንዣብብ አድርጓል።
ህወሓት ራሱ ለጦርነት እየተዘጋጀ መሆኑን በይፋ ባይገልጽም፣ የፌደራል መንግሥቱ፣ የትግራይ ተቃዋሚ ኃይሎች እና ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ግን ፓርቲው ለጦርነት ዝግጅት እያደረገ ነው የሚሉ ወቀሳዎችንና ሪፖርቶችን እያወጡ ይገኛሉ።
ከፍተኛ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናት እና ብሔራዊ የመረጃና ደኅንነት አገልግሎት ባወጡት መረጃ ህወሓት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ወታደራዊ ጥቃት ለመሰንዘር እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ከሰዋል። የፌደራል ባለሥልጣናት ህወሓት ከኤርትራ መንግሥት ጋር በመቀራረብ ሴራ እየሸረበ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል የሚታየው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላም አንዱ የጦርነት ዝግጅት መሆኑ ተመልክቷል፡፡ የትግራይ ክልል ምክር ቤት በቅርቡ የግዳጅ ወታደራዊ አገልግሎት አዋጅ ማውጣቱን ተከትሎ፣ ሂውማን ራይትስ ዋች (Human Rights Watch) እና የአውሮፓ ሕብረት አዋጁ እንዲሰረዝ አሳስበዋል። በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የወጣቶች አፈሳና አስገዳጅ ወታደራዊ ምልመላዎች እየተካሄዱ መሆኑ በስፋት ሪፖርት ተደርጓል።
የትግራይ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ፡፡ እንደ የትግራይ ነጻነት ፓርቲ፣ ባይቶና እና ዓረና ያሉ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ህወሓት አዳዲስ ተዋጊዎችን በመመልመል እና ነባር የትግራይ መከላከያ ኃይል (TDF) አባላትን በማንቀሳቀስ ለዳግም ጦርነት እየተዘጋጀ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ህወሓት የሀብት እና ገንዘብ ማሰባሰብ ተግባር ላይ ማተኮሩም እየተነገረ ነው፡፡ በክልሉ ከሠራተኞች ደሞዝ መቁረጥን ጨምሮ ለጦርነት ዝግጅት የሚውሉ የገንዘብና የስንቅ ማሰባሰብ ሥራዎች በግዳጅ እየተከናወኑ መሆኑን የአገር ውስጥ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።
በትግራይ ነዋሪ የሆነዉ ደሞዝተኛ ሕዝብ የአንድ ወር ደምወዙን እንዲያዋጣ፤ ደመወዝተኛ ያልሆነዉ ደግሞ ሌሎች ቁሳቁሶችን እንዲሰጥ መጠየቁን በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞ አሰምተዋል። በሌላ በኩል በትግራይ ይቀሰቀሳል የተባለዉን ግጭት ፈርተዉ የትግራይ ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ ወጣቱ አካባቢዉን ለቆ እየወጣ እንደሆነ ተሰምቷል።
ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ስድስት ቢሊዮን ብርን ለማሰባሰብ ሰራተኛዉ ሕዝብ የአንድ ወር ደመወዙን እንዲሰጥ እያስገደደ መሆኑን አካባቢዉ ላይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች በጽኑ አዉግዘዋል።
በትግራይ ነዋሪ የሆነዉ ደሞዝተኛ ሕዝብ የአንድ ወር ደምወዙን በግድ እንዲያዋጣ የሚያስገድደዉ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሌላ በኩል ደግሞ ፌደራል መንግሥት ለሰራተኛዉ ደምወዝ አላከም ሲል እየከሰሰ ነዉ ሲሉ ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነት እና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አምዶም ገብረሥላሴ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«የህወሓት አስተዳደር የገንዘብ ማሰባሰብ ፕሮግራም አለን፤ ብሎ ስድስት ቢሊየን ብር እንደሚሰበሰብ በይፋ ካስታወቀ አንድ ወር ገደማ ሆኖታል። ይህን ገንዘብ የሚያሰባስበዉ ከመንግሥት ሰራተኛዉና ከነጋዴው ነዉ ሲል ቀጭን ትዕዛዝ አስተላልፏል። የመንግሥት ሰራተኛዉ አናዋጣም ብሎ ከፍተኛ ተቃዉሞ ቢያሰማም፤ መመርያ ነዉ ብሎ የግድ መክፈል አለባችሁ ሲል ትዕዛዙን አስተላልፏል።»
ህወሓት ይህ መዋጮ መደረግ አለበት ሲል እንደምክንያት የተጠቀሰዉ ባለፈዉ የትግራይ ጦርነት ላይ፤ ጉዳት የደረሰባቸዉ አካል ጉዳተኞች ህክምና እና እንክብካቤ እንዲያገኙ ለማድረግ ነው ሲል ህዝቡን የማዘናጊያ ምክንያት ሰጥቷል።
ህወሓት ለጦርነቱ ከሻብያና ከፋኖ ኃይሎች ጋር የመሠረተው ፅምዶ የተባለዉ ወታደራዊ ጥምረት ጋር ወታደራዊ ዝግጅቶችን እያካሄደ እንደሚገኝ ተመልክቷል። ገንዘቡን የሚያሰባስበዉ በዋናነት በቀጣይ ለመጀመር ላቀደው ጦርነት ነዉ። በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ይህንን የህወሓትን እርምጃ አውግዘዋል።














