የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አዲስ አበባ አዲስ አበባ መግባታቸውን የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፤ ላቭሮቭ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ አቀባበል ያደረጉላቸው በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የአውሮፓና አሜሪካ ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አምባሳደር መለስ ዓለም ናቸው።
ይህ ጉብኝት የተከናወነው ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) ሙሉ አባል መሆኗን ተከትሎ ኢትዮጵያና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከራቸውን በቀጠሉበት ወቅት ሲሆን ይህም ላቭሮቭ እ.ኤ.አ በሐምሌ 2022 በአዲስ አበባ ባደረጉት ጉብኝታቸው ወቅት ከተወያዩባቸው ዘርፎች ባሻገር ትብብሩን የሚያሰፋ ነው።
የሩሲያው መንግሥታዊ የዜና ወኪል ታስ (TASS) እንደዘገበው፤ ላቭሮቭ ዛሬ ማክሰኞ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ እና ከሌሎች ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ውይይቶቹ በሁለትዮሽ ግንኙነቶች፣ በብሪክስ ማዕቀፍ ውስጥ በሚደረጉ ትብብሮች እንዲሁም በተለያዩ ቀጠናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ ታስ ዘግቧል።
ላቭሮቭ እ.ኤ.አ. በ2022 ካደረጉት ጉብኝት ወዲህ ኢትዮጵያ የብሪክስ ሙሉ አባል በመሆን የተቀላቀለች ሲሆን፥ በካዛን በተካሄደው የጥምረቱ ጉባኤ ላይ መሳተፏ ይታወሳል። ይህ አዲስ ምዕራፍ በአዲስ አበባ እና በሞስኮ መካከል ያለውን የትብብር አድማስ ይበልጥ አስፍቶታል።
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቀደም ሲል እንደገለጸው፤ ሩሲያ እና ኢትዮጵያ በብዙ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ የተቀራረበና ተመሳሳይ አቋም ያላቸው በመሆኑ በባለብዙ ወገን መድረኮች ላይ በጋራ ለመሥራት አስችሏቸዋል።
ታስ አክሎ እንደዘገበው፤ ላቭሮቭ ለኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ስለ ዩክሬኑ ጦርነት ወቅታዊ ሁኔታዎች ማብራሪያ ይሰጣሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፥ በመጪው ጥቅምት ወር በሞስኮ እንዲካሄድ ስለታቀደው ሦስተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ዝግጅት ላይም ምክክር ያደርጋሉ።














