የፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ ወደ ግል ይዞታነት መዘዋወሩን እና የአስተዳደር ቁጥጥሩ በአሪፍ ሀቢብ ግሩፕ ለሚመራው ጥምረት መሰጠቱን ተከትሎ፥ የቀድሞው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ተመረጡ።
ይህ ሹመት ኪሳራ ውስጥ የሚገኘውን አየር መንገድ በአዲስ ኢንቨስትመንት በሚታገዙ የበረራ ዝመና፣ የኔትወርክ ማስፋፊያ እና የአሠራር ማሻሻያዎች አማካኝነት መልሶ እንዲያንሰራራ የሚደረገውን ጥረት ያግዛል ተብሎ ይጠበቃል።
ቀደም ሲል ብሉምበርግ ለጉዳዩን ቅርበት ያላቸውን ሰዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ አቶ ተወልደ ለዚህ የሥራ መደብ እጩ ሆነው ከቀረቡ ሰዎች መካከል ሲሆኑ፤ አስፈላጊው ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ ይፋዊ መግለጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል። አረብ ኒውስ በበኩሉ አየር መንገዱ የደኅንነት ማረጋገጫዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ ይፋዊ መግለጫ ከመስጠት መቆጠቡን ዘግቧል።
ስማቸው ያልተጠቀሰ ምንጮችን የጠቀሰው አረብ ኒውስ፥ አንድ ከፍተኛ የአየር መንገዱ ባለሥልጣን አየር መንገዱ «ሁሉም የደኅንነት ማረጋገጫዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ ስማቸውን ይፋ እንደማያደርግ» ማረጋገጣቸውን አስታውቋል። አንድ ከፍተኛ የአየር መንገዱ ኃላፊ ደግሞ አቶ ተወልደ «እጅግ ብቁ ሰው» እና «በርካታ መልካም ለውጦችን ያመጡ» መሆናቸውን ገልጸዋል።
አቶ ተወልደ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ በጤና ምክንያት ጡረታ እስከወጡበት 2022 ድረስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው አገልግለዋል። በኃላፊነት ዘመናቸው ትላልቅ የበረራ አውሮፕላኖችን ቀጥር በማስፋፋት፣ የበረራ መስመሮችን በማሳደግ እና አዲስ አበባን አህጉራዊ የአቪዬሽን ማዕከል በማድረግ አየር መንገዱ የአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ ወደ መሆን እንዲሸጋገር አድርገዋል።
በወቅቱ በጤና እክል ምክንያት ሥልጣናቸውን የለቀቁ ሲሆን፥ ለአንድ ዓመት ያህል በሕክምና ክትትል ላይ እንደነበሩና በዩናይትድ ስቴትስ ለበርካታ ወራት ሕክምና ሲከታተሉ መቆየታቸውን፣ ይህም ሥራው የሚፈልገውን በአካል ተገኝተው አመራር ለመስጠት አስቸጋሪ እንዳደረገባቸው መግለጻቸው ይታወሳል።














