ትግራይ ውስጥ ህወሓት የሚያካሂደውን አፈሳ በይፋ የተቃወሙ ሁለት የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃነ ጳጳሳት፥ ከግድያ ሙከራ መትረፋቸው ከተገለጸ ጥቂት ቀናት በኋላ በአክሱም ከተማ በቁም እስር ላይ መሆናቸው ተገለፀ።
የሃይማኖት አባቶቹ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በፖሊስ ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ተወስነው እንደሚገኙ ምንጮች ገልጸዋል።
በቁም እስር ላይ የሚገኙት አባቶች የሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ናትናኤል እና የትግራይ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ አረጋዊ ናቸው።
ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደገለጹት፥ ሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ቅዳሜ ሐምሌ 4 ቀን 2018 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ በአክሱም ወደሚገኝ የፖሊስ ጣቢያ ለጥያቄ ተወስደው ለበርካታ ሰዓታት ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ በዚያው ዕለት ምሽት ተለቀዋል።
ነገር ግን ሊቃነ ጳጳሳቱ ከእስር ቢፈቱም፥ ወደ ቀድሞ ነጻነታቸው አልተመለሱም። ሊቃነ ጳጳሳቱ በጽዮን ማርያም ቤተ ክርስቲያን አቅራቢያ ወደሚገኘው የመንበረ ሰላማ ቅጥር ግቢ እንዲመለሱ ተደርገው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በቁም እስር ላይ እንደሚገኙ ምንጮቹ አስረድተዋል።
«በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ተወስነው ይገኛሉ፤ ማንም ሰው እንዲገባ ወይም እንዲወጣ አይፈቀድም» ሲል አንድ ምንጭ ለአዲስ ስታንዳርድ ገልጿል።
እንደ ምንጮቹ ገለጻ፥ በቅጥር ግቢው ዙሪያ የፖሊስ አባላት የተሰማሩ ሲሆን፥ ሊቃነ ጳጳሳቱ እንዳይወጡ እንዲሁም ጎብኚዎች ወደ ግቢው እንዳይገቡ እየከለከሉ ይገኛሉ። ሊቃነ ጳጳሳቱን ለመጠየቅ የሞከሩ የቅርብ ወዳጆቻቸው ግቢውን በሚጠብቁ ፖሊሶች እንዲመለሱ የተደረጉ ሲሆን፤ ፖሊሶቹም እገዳው የተጣለው «ከበላይ አካል በተሰጠ ትዕዛዝ» መሆኑን እንደነገሯቸው ገልጸዋል።
የቤተ ክርስቲያኒቱ ሠራተኞች መደበኛ የአስተዳደር ሥራዎችን ለማከናወን ወደ ቅጥር ግቢው እንዲገቡ ቢፈቀድላቸውም፥ ከሁለቱ ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ግን እንዲገናኙ እንደማይፈቀድላቸው ምንጮቹ አክለው ገልጸዋል። በዚህም ምክንያት የቅርብ ሰዎቻቸው ሊቃነ ጳጳሳቱ በአሁኑ ወቅት በምን ዓይነት ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ማወቅ እንዳልቻሉ ይናገራሉ።














