ሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ የሚፈፅመውን አፈና እና ጭቆና የሚያወግዝ ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በዛሬው ዕለት ቅዳሜ ሐምሌ 11/2018 ተካሂዷል።
በትግራይ የሰላምና ለውጥ ምክር ቤት ”አፈሳ ይቁም፥ ሰላም ይስፈን” በሚል መሪ ሃሳብ በተዘጋጀው በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በአዲስ አበባ እና በአካባቢው የሚኖሩ የትግራይ ክልል ተወላጆች፣ የሲቪክ ማህበራት፣ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ይገኛል።
ሰልፉ ሕገ-ወጥ ቡድኑ በትግራይ ክልል ወጣቶች ላይ የሚፈፅመውን አስገዳጅ ወታደራዊ ምልምላ እና እየደረሰ ያለውን ሰብዓዊ ጉስቁልና እንዲሁም ሥነ-ልቦናዊ ጫና በፅኑ የሚቃወም ነው።
በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ የሚካሄደውን ሰልፍ ያዘጋጀው ግንቦት ላይ የተቋቋመው “የትግራይ ሰላም እና ለውጥ ምክር ቤት” እንደሆነ የሚዲያ እና ሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪው ከበደ አሰፋ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ከሁለት ወር በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የተመሠረተው ይህ ምክር ቤት በትግራይ የክልላዊ መንግሥት ለውጥ ለማምጣት እንደሚሠራ እና የሽግግር ሂደቶችን ለማመቻቸት እንደሚንቀሳቀስ ይገልጻል።
ምክር ቤቱ በውስጡ ከህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የተለዩ እና የተቃረኑ ፖለቲከኞች እንዲሁም የትግራይ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ይዟል።
በምክር ቤቱ ሥር የተቋቋሙ ኮሚቴዎችን የሚመሩት ጄነራል ጻድቃን ገብረትንሳይ ናቸው። በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የምሥራቅ አፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ጌታቸው ረዳ የሚመራው ዴሞክራሲያዊ ስምረት ትግራይ ፓርቲ (ስምረት) ከምክር ቤቱ አባላት አንዱ ነው።
ከህወሓት በተለዩ አመራሮች የተመሠረተው ሌላኛው ፓርቲ ወለዶ ትግራይ፣ አረና ትግራይ ለዴሞክራሲ እና ሉዓላዊነት (አረና) እንዲሁም ትንሳኤ ሰባ እንደርታ ተጠቃሽ ናቸው።
የትንሳኤ ሰባ እንደርታ ሊቀ መንበር እና የምክር ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት አስተባባሪ የሆኑት አቶ ከበደ እንደሚናገሩት ቅዳሜ ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም ሊካሄድ የታቀደው ሰልፍ ሁለት ዋነኛ ዓላማዎች አሉት። በቀዳሚነት የጠቀሱት በክልሉ የሚካሄደውን “የግዳጅ ወታደራዊ አፈሳ” ነው።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) እንዲሁም ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም ሂውማን ራይትስ ዎች ባወጧቸው መግለጫዎች በክልሉ የሚካሄደው የግዳጅ ወታደራዊ ምልመላ እንዲቆም መጠየቃቸው ይታወሳል።














