ሳዑዲ_አረቢያ በቀይ ባሕር አዲስ የባሕር ኃይል ጥምረት መቋቋሙን ገለፀች፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኦማን ከጥምረቱ ውጪ ሆነዋል፡፡
የየመን ሁቲዎች የሚያካሂዱትን ጥቃት ተከተሎ፣ ሳዑዲ አረቢያ በቀይ ባሕር፣ በባብ ኤል-ማንደብ መደብ እና በኤደን በህረ-ሰላጤ በኩል የሚያልፉ የንግድና የኃይል ማጓጓዣ መስመሮችን ለመጠበቅ ያለመ የባሕር ኃይል መከላከያ ጥምረት ማቋቋሟን አስታወቀች።
የሳዑዲ አረቢያ መከላከያ ሚኒስቴር ይህንን ውሳኔ ይፋ ያደረገው ከ43 ሀገራት የተወጣጡ የመከላከያ ተወካዮች እና የአውሮፓ ሕብረት ልዑካን በታደሙበት ስብሰባ ላይ ነው። ሪያድ አዲሱን ጥምረት የምትመራ ሲሆን ዋና መስሪያ ቤቱም በዚያው እንደሚሆን ተገልጿል። ይህ ጥረት የባሕር ደኅንነትን ለማጠናከር፣ የነጻ የባሕር ላይ ጉዞን ለማረጋገጥ እና ዓለም አቀፍ የንግድና የኃይል አቅርቦቶችን ለመጠበቅ ያለመ መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል።
ይህን ማዕቀፍ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኩዌት፣ ባህሬን፣ ካታር፣ ፓኪስታን፣ ቱርክ፣ ግብፅ፣ ዮርዳኖስ፣ የመን፣ ባንግላዴሽ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ጂቡቲ እና ሶማሊያ ጨምሮ 14 ሀገራት በይፋ ደግፈውታል። ጥምረቱ የጋራ እቅድ፣ ልምምዶችን፣ የመረጃ ልውውጥን እና የተቀናጁ የባሕር ላይ እንቅስቃሴዎችን የሚያካትት መከላከያ ነክ ስምምነት ሲሆን፣ በየትኛውም እንቅስቃሴ ላይ መሳተፍ የየሀገራቱ የሉአላዊነት ውሳኔ ሆኖ ይቀጥላል።
ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ ትብብር ምክር ቤት (GCC) ስድስት አባል ሀገራት መካከል ሁለቱ ማለትም የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ እና ኦማን አለመካተታቸው ትኩረት ስቧል። የሁለቱ ሀገራት ከጥምረቱ ውጪ መሆን በቀጠናው ባላቸው ስትራቴጂካዊ ቦታ እና የባሕር ደኅንነት ፍላጎቶች አንጻር ከፍተኛ ትርጉም ያለው መሆኑን ሮይተርስ አመልክቷል።
ይህ ጅማሮ ሁቲዎች በሳዑዲ አረቢያ ላይ የባሕር ላይ እገዳ መጣላቸውን ካወጁ እና በቀይ ባሕር በሚንቀሳቀሱ የሳዑዲ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ የመጣ ነው። ሳዑዲ አረቢያ በበኩሏ በየመን በሚገኙ የሁቲ ወታደራዊ ተቋማት ላይ የአየር ጥቃቶችን ስታካሂድ ቆይታለች።
ይህ አዲስ ስብስብ የአውሮፓ ሕብረት የሚያካሂደውን «ኦፕሬሽን አስፒደስ» ጨምሮ ከነባር የምዕራባውያን የባሕር ደኅንነት ስራዎች ጎን ለጎን የሚሰራ ቢሆንም፣ የጥምረቱ ዝርዝር ተልዕኮ፣ የተቋማዊ መዋቅር እና ከነባር ተልዕኮዎች ጋር የሚኖረው ግንኙነት ወደፊት የሚወሰን ይሆናል።














