አሜሪካ በርካታ ቢሊዮን ዶላር ወጪ ለሚጠይቀው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኝነቷን በድጋሚ አረጋገጠች። ፕሮጀክቱን ዕውን ለማድረግ ቦይንግ እና ጂኢ ኤሮስፔስ የመሳሰሉ የአሜሪካ ኩባንያዎች ከፍተኛ ተሳትፎ እንዲኖራቸው መንገዶችን እያሰሰች መሆኑን ገልጻልች።
በአዲስ አበባ ከተካሄደው የአፍሪካ ሎጂስቲክስ እና ኮሙኒኬሽን ሲምፖዚየም (ALCS26) በኋላ ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. በተሰጠው ዲጂታል ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ንግግር ያደረጉት የአሜሪካ ንግድ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅና አፍሪካ ምክትል ረዳት ሚኒስትር ማርክ ሚቼል፥ ከኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ አመራሮች እና ከግል ዘርፉ ተወካዮች ጋር ያደረጉት ውይይት ኢትዮጵያ ለአሜሪካ ባለሀብቶች የንግድ ዕድል የምትሰጥ መሆኗን ያረጋገጠ ነው ብለዋል።
ሚቼል ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ያደረጉት ውይይት ጉብኝታቸው ወሳኝ እንደነበር ገልጸዋል። «ለድርጅቱም ሆነ ለአገሪቱ እጅግ ድንቅ እና አስደሳች ሥራ በሆነው የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ዙሪያ በስፋት ተወያይተናል» ሲሉ ተናግረዋል። አክለውም «የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በተለያዩ ተቋማቱ በኩል ይህንን ለውጥ አምጪ ፕሮጀክት ዕውን ለማድረግ የሚደግፍበትን መንገድ ለማሰስ ቁርጠኛ ነው» ያሉ ሲሆን፥ የንግድ መምሪያው የአሜሪካ ኩባንያዎች ጠንካራ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በቅርበት እየሰራ መሆኑንም አብራርተዋል።
ሚቼል አክለውም በቦይንግ እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ መካከል ያለው የቆየ አጋርነት «ለአሜሪካ እና ለኢትዮጵያ አሁንም የኩራት ምንጭ ነው» ብለዋል። «የዚህ አውሮፕላን ማረፊያ መስፋፋት ለአየር መንገዱ እድገት የሚያበስረውን መልካም አጋጣሚ በማየታችን ደስ ተሰኝተናል፤ ይህም ማለት በጂኢ ኤሮስፔስ ሞተሮች የሚሰሩ ተጨማሪ የቦይንግ አውሮፕላኖች አፍሪካን ከቀረው ዓለም ጋር በይበልጥ ያገናኛሉ ማለት ነው» ሲሉ ገልጸዋል።
ይህ አስተያየት የተሰጠው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአፍሪካ ትልቁ የአቪዬሽን ማዕከል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀውን የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ እቅድ እያፋጠነ ባለበት ወቅት ነው።
ከአዲስ አበባ በስተደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው አቡሰራ ቢሾፍቱ የሚገነባው ይህ አውሮፕላን ማረፊያ፥ በዛሃ ሀዲድ አርክቴክቶች የተነደፈና አራት ትይዩ የመንደርደሪያ መስመሮች (runways) ያሉት ሲሆን፥ በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ያለውን ከፍተኛ መጨናነቅ ያቃልላል ተብሎ ይጠበቃል።
አየር መንገዱ የመጀመሪያው ምዕራፍ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት 60 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም የሚኖረው ሲሆን፥ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ደግሞ 110 ሚሊዮን መንገደኞችን እና አራት ሚሊዮን ቶን ጭነት የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል። የፕሮጀክቱ ግንባታ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጥር 2 ቀን 2018 ዓ.ም. የመሰረት ድንጋይ ካስቀመጡ በኋላ በይፋ የተጀመረ ሲሆን፥ በ2021 ዓ.ም (በፈረንጆች 2029) ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
አዲሱ የአሜሪካ መግለጫ ዋሽንግተን ቀደም ሲል ለፕሮጀክቱ ያሳየችውን ድጋፍ የሚያጠናክር ነው። በታህሳስ 2018 ዓ.ም የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ከፍተኛ አማካሪ ማሳድ ቡሎስ፥ ዩናይትድ ስቴትስ የ10 ቢሊዮን ዶላር ወጪ የሚጠይቀውን የአውሮፕላን ማረፊያ ልማት እንደምትደግፍ አስታውቀዋል። አክለውም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ፋይናንስ ኮርፖሬሽን (DFC) ከቦይንግ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ አየር መንገድ እና በሌሎች የአፍሪካ ፕሮጀክቶች ላይ እየሰራ መሆኑን ገልጸው ነበር።
ፕሮጀክቱ የበርካታ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን ትኩረትስቧል። ነሐሴ 2017 ዓ.ም የአፍሪካ ልማት ባንክ (AfDB) የወደፊቱ የአፍሪካ ትልቁ አውሮፕላን ማረፊያ ሲል የገለጸውን ይህንኑ ፕሮጀክት ለመደገፍ 8 ቢሊዮን ዶላር ለማሰባሰብ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር ስምምነት መፈራረሙ ይታወሳል። ሆኖም ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ይፋ የተደረገ የመጨረሻ የፋይናንስ ስምምነት የለም።
ይህ ሁኔታ ሐምሌ 22 ቀን 2018 ዓ.ም. በድጋሚ የተረጋገጠ ሲሆን፥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ከአበዳሪዎች በኩል ያለው «የፍላጎት መግለጫ» ብቻ እንደሆነና ለአውሮፕላን ማረፊያው እስካሁን የተፈረመ ወይም የተጠናቀቀ የብድር ስምምነት አለመኖሩን ተናግረዋል።
ሐምሌ 22 ቀን በተካሄደው የአየር መንገዱ ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም መግለጫ ወቅት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው፥ የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በግምት 9 ቢሊዮን ዶላር የጋራ ፋይናንስ (syndicated financing) የሚጠይቅ መሆኑንና ገንዘቡም ከአንድ ተቋም ይልቅ የዓለም አቀፍ አበዳሪዎች ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
አቶ መስፍን አክለውም በአየር መንገዱ የተዘጋጀውን የአዋጭነት ጥናት (feasibility study) ከተቀበሉ በኋላ ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከአዥያ፣ ከመካከለኛው ምስራቅ እና ከሩቅ ምስራቅ የመጡ የፋይናንስ ተቋማት ፕሮጀክቱን በፋይናንስ ለመደገፍ ፍላጎታቸውን ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
አበዳሪ ተቋማት ማንኛውንም የፋይናንስ ውል ከመወሰናቸው በፊት የራሳቸውን ጥልቅ ግምገማ (due diligence) እና የአገር ውስጥ ጥናት ያካሂዳሉ ያሉት አቶ መስፍን፥ በርካታ ተቋማት ቀደም ብለው የግምገማ ሂደቱን መጀመራቸውን ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል ከአበዳሪዎች ጋር በተደረጉ ውይይቶች እስከ 8.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የፋይናንስ ፍላጎት መታየቱን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፥ ይህም የፋይናንስ ማሰባሰብ ሂደቱን በማስተባበር ላይ የሚገኘው የአፍሪካ ልማት ባንክ እስከ 500 ሚሊዮን ዶላር ለማበርከት የገባውን ቃል ጨምሮ መሆኑን አብራርተዋል።
ሆኖም አቶ መስፍን እስካሁን የተፈረመ ወይም ያለቀ የፋይናንስ ስምምነት አለመኖሩን አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩ ሲሆን፥ እያንዳንዱ ተቋም የውስጥ ግምገማውን እስኪያጠናቅቅ ድረስ በአበዳሪዎች በኩል የሚታየው ፍላጎት ህጋዊ አሳሪ አለመሆኑን ገልጸዋል። አበዳሪዎቹ እስከ መጋቢት 2019 ዓ.ም ድረስ የመጨረሻ የፋይናንስ ውሳኔያቸውን ያስታውቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅና የአፍሪካ ልማት ባንክም የጋራ ብድር (syndicated loan) ሂደቱን ማስተባበሩን እንደሚቀጥል አክለው ገልጸዋል።














