በትግራይ ክልል ግጭት ማገርሸቱ ነዋሪዎችን “እንደ አዲስ ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰት አጋልጧል” ሲል አስጠነቀቀ። የፌደራል መንግሥት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት እንደ የንጹኃንን ደኅነንት ማስጠበቅ ላሉ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች መርሆዎች እንዲገዙም ጠይቋል።
ሥለ ቅዳሜዉ የሸረሪና ዉጊያ፣ የህወሓት የክተት ጥሪና የፌዴራል መንግሥት ዝምታ ብዙ እየተባለ ይገኛል፡፡ የመንግሥት የካቢኔ አባል ማረጋገጪያና የመንግሥት ደጋፊዎች የቃላት ዘመቻ ቢደጋገምም ውጊያዉ ቢያንስ እስከ ዛሬ የቀጠለ አይመስልም። ከእንግዲሕ ላለመቀጠሉ ግን ምንም ዋስትና የለም፡፡
“የፕሪቶሪያ ሥምምነት ምን እንቅፋት ገጠመው?” ጥቅምት 2015 ከወደ ፕሪቶሪያ ደቡብ አፍሪቃ አፅናኝ ቃል ተሰምቶ ነበር።የተለያዩ ወገኖች እንደገመቱት ከአንድ ሚሊዮን በላይ ያለቁ፣ ሚሊዮኖች አካላቸዉ የጎደለ፣ሴቶች የተደፈሩ፣ ብዙ ሚሊዮኖች የተፈናቀሉበት ዘግናኝ ጦርነት ፍፃሜ ተነግሮ ለቀሪዎች የሰላም ተስፋ ፈንጥቆ ነበር። የጠመንጃዉ ላንቃ ተዘጋ-የአፍሪቃ ህብረት አደራዳሪዎች ቡድን መሪ ኦሌ ሴጎን ኦባሳንጆ እንዳሉት።
«ዛሬ ለኢትዮጵያ አዲስ ጎሕ ቀደደ፣ ለምስራቅ አፍሪቃ፣ በርግጥ ለመላዉ አፍሪቃም አዲስ ጎሕ ቀደደ። ይሕ ለአፍሪቃ ችግሮች የአፍሪቃ መፍትሔ (አብነት) ነዉ። በዛሬዉ የሰላም ስምምነት (የአፍሪቃ ሕብረትን) አጀንዳ 2063 አካል የሆነዉ ገቢር ሲደረግ አይተናል። ይህም አፍሪቃ ዉስጥ የጠመንጃ ላንቃን ማዘጋት ነዉ። በኢትዮጵያዉ ግጭት የሚዋጉ ሁለቱ ወገኖች ግጭቶችን ለማቆም በይፋ ተስማምተዋል።» ሲሉ ኦባሳንጆ አብስረዋል፡፡
ይሕ ቃል፣ ይሕ ተስፋ፣ይህ የአፍሪቃ አብነት ስምምነት ይዘት፣ ሒደትና ገቢራዊነቱ ገና ከጅምሩ ማወዛገብ፣ ማከራከር፣ ማሻኮት-አልፎ አልፎ ማጋጨቱም አልቀረም።የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዲፕሎማትና የሕግ ባለሙያ ባይሳ ዋቅወያ እንደሚሉት አክራሪ የትግራይ ፖለቲከኛና የጦር አዛዦች ስምምነቱን እንደ ሽንፈት ሥለቆጠሩት ገና ከጅምሩ ለገጠመው ፈተና አንዱ ምናልባትም ዋናዉ ምክንያት ነው።
ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ከአማራ መገናኛ ብዙሐን ጋር በነበራው ቃለመጠይቅ እንደተነገሩት «የፕሪቶሪያ ሥምምነት ለትግራይ፣ ለአማራ፣ ለአፋር በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ያስገኘዉ ነገር የተኩስ ድምፅ እንዳንሰማ ማድረግና አንፃራዊ በሆነ መንገድ ወደ ልማት እንድናተኩር ማድረግ ነዉ» ብለዋል፡፡
የጠቅላይ ሚንስትሩ መልዕክት ተተንትኖ-ምናልባትም ተደምጦ ሳያበቃ ግን ሸረሪና, ምዕራብ ትግራይ ጦርነት መጀመሩ ከመቀሌ ታወጀ። ህወሓት መራሹ የትግራይ ክልላዊ መንግስት ባወጣዉ መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ጦርና የትግራይ ኃይል የሚባለዉ የህወሓት ታጣቂዎች ቅዳሜ ሐምሌ 25፣ 2018 ከማለዳዉ እስከ ቀትር ድረስ ሲዋጉ ነበር።
በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያ የተሰራጨዉ መግለጫ «የትግራይ ሕዝብን ለማጥፋት ያለመ ጦርነት» ያለዉን ግጭት ለመመከት የትግራይ ሕዝብ በሙሉ የኃይማኖት ተቋማት ሳይቀሩ እንዲዘጋጁ ጥሪ አድርጓል።
«በሐገር ዉስጥና በዉጪ የምትኖር የትግራይ ሕዝብ፣ ዲያስፖራዎች፣ ሁሉም የትግራይ ሠራዊትና የፀጥታ አካላት፣ የትግራይ ብሔራዉያን ኃይሎች፣ የትግራይ ሲቪል ማሕበራት፣ የትግራይ ኃይማኖታዊ ተቋማት ጥሪ እናቀርባለን» ሲል ክተት አውጇል፡፡
ፌዴራል መንግሥት ስለቅዳሜው ግጭትም ሆነ፣ የትግራይ ክልልላዊ መንግሥት ስላደረገዉ «የክተት» አይነት ጥሪ እስካሁን በይፋ ያለዉ ነገር የለም። በትግራዩ ጦርነት ወቅት የትግራይ ክልልን የሽግግር አስተዳደርን ላጭር ጊዜ የመሩት፣ ኋላ የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስርትርና አሁን የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር አብረሐም በላይ ግን ግጭቱ መቀስቀሱን አስታውቀዋል።
ቅዳሜ የተቀሰቀሰው ግጭት እሁድ ዕለትም ቀጥሎ የነበረ ሲሆን ይህ ግጭት “በከባድ መሣሪያ እና ድሮን” የታገዘ እንደነበር አንድ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) ምንጭ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል። የዓይን እማኞችም ቅዳሜ ዕለት ፍንዳታዎችን፣ የከባድ መሣሪያ ተኩስ እና የአውሮፕላኖችን ድምጽ ሲሰሙ እንደነበር ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን ሥልጣን በህገወጥ መነወገድ የተቆጣጠረው እና በህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የክልሉ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ፣ ፌደራል መንግሥት “ግልፅ ጦርነት ከፍቷል” ሲል ከስሷል።
የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር እንዲሁም የገዢው ብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት ዶ/ር አብርሃም በላይ ከሱዳን ጋር በሚያዋስነው ሥፍራ ግጭት መነሳቱን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የህወሓት ኃይሎች “ጦርነት እንደከፈቱ” ከስሰው፤ “ይህ ጦርነት ከወዲሁ ካልቆመ. . .የከፋ ጉዳት ይከተላል” በማለት አስጠንቅቀዋል። ከዚህ ክስተት በኋላ ትናንት ምሽት መግለጫ ያወጣው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ክልሉ ዳግም ወደ ግጭት መግባቱ የፈጠረውን ስጋት ገልጿል።
በአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ቲጌሬ ቻጉታህ፤ “በትግራይ በድጋሚ ግጭት መጀመሩ ነዋሪዎችን እንደ አዲስ ለሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ያጋልጣቸዋል” ብለዋል። ማኅበረሰቦች ከዚህ ቀደም ለተፈጸሙ ጥሰቶች “ፍትሕ እና ተጠያቂነት” አለማግኘታቸውንም ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል።
አሁን ውጊያ ያገረሸው “በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች የትጥቅ ግጭቶች” በቀጠሉበት ሁኔታ መሆኑን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት የምርመራ መንገዶችን መዘርጋት” እንደሚያስፈልግም ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ተቋም በአማራ እና ኦሮሚያ ክልሎች ካሉት ግጭቶች ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ “ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን እና በደሎችን መመዝገብ መቀጠሉን” አንስተዋል።
በትግራይ ጦርነት ወቅትም “የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ተብለው ሊፈረጁ የሚችሉ ከባድ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን” መሰነዳቸውን አስታውሰዋል። ዋና ዳይሬክተሩ “ኢትዮጵያ ተአማኒነት ያላቸው ምርመራዎች እና ጥፋት ፈጻሚዎች ላይ የሚካሄዱ የክስ ሂደቶች አለመኖርን በጭራሽ እንደ መደበኛ ነገር መውሰድ የለባትም” እንዳሉ መግለጫው ያስረዳል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ “የፌደራል እና የትግራይ ባለሥልጣናት የንጹኃን ጥበቃን ጨምሮ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ደረጃዎችን እንዲያከብሩ እና [ለእነርሱ] እንዲገዙ” ጥሪ አቅርቧል። ባለሥልጣናቱ፤ ለገለልተኛ የሰብአዊ መብቶች ተከታታዮች እና የሰብዓዊ ድጋፍ ተዋናዮች በእነዚህ አካባቢዎች “ያልተገደበ እንቅስቃሴ” እንዲፈቀድላቸውም ጠይቋል።














