ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች ጀምሮ እየመሯት የሚገኙት ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፤ የፖለቲካ ለውጦችን እንዲያካሂዱ በይፋ ጥያቄ ያቀረቡት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በቁጥጥር ስር አውለዋል፤ ደብዛቸው ከጠፋም 25 ዓመታት ተቆጥረዋል።
ቡድን 15 (ጂ15) የሚባሉት ባለሥልጣናት በነጻነት ትግሉ እና ከዚያም በኋላም በተለያዩ ከፍተኛ የሥልጣን ደረጃ ላይ የነበሩ ሲሆን፣ በአገሪቱ ውስጥ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲደረግ በግልጽ ከጠየቁ በኋላ መስከረም 8/1994 ዓ.ም ለእስር ተዳርገው አስካሁን ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም።
በነጻነት ትግሉ እና በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ባለስልጣናቱ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ምርጫ እንዲያካሄዱ፣ አገሪቱም በሕገ መንግሥት እንድትተዳደር የሚጠይቅ ግልጽ ደብዳቤ ጽፈው በይፋ አሠራጭተው ነበር።
ፕሬዝዳንቱ ለውጥ እንዲያደርጉ በደብዳቤ ጥያቄ ካቀረቡት 15 ባለሥልጣናት መካከል 11ዱ በኤርትራ የፀጥታ ኃይሎች ወዲያውኑ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፤ አራቱ መስፍን ሓጎስ፣ ኣድሓኖም ገብረማርያም፣ ኃይለ መንቀርዮስ እና መሓመድ ብርሃን ሳይያዙ ቀርተው በስደት ላይ ይገኛሉ።
ለእስር የተዳረጉት እነዚህ ባለሥልጣናት ክስ ሳይቀርብባቸው፣ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ፣ የት እንዳሉ ሳይታወቅ እነሆ 25 ዓመት ሞላቸው። በእስር ላይ የሚገኙት ባለሥልጣናት ያሉበትን ሁኔታ በተመለከተ በተለያዩ ጊዜያት ከተለያዩ ምንጮች ከሚወጡ መረጃዎች በስተቀር ምንም ዓይነት አስተማማኝ ነገር የለም።
የኤርትራ መንግሥት ግን ታሳሪዎቹ በድንበር ይገባኛል ምክንያት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ባካሄደበት ጊዜ የአገሪቱን ነፃነት እና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ተግባራትን ፈጽመዋል፣ ከህወሓት መሪዎች ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል በሚል ይፋዊ ያልሆነ “የአገር ክህደት” ክስ ያቀርብባቸዋል።
የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናቱ በተያዙ ማግስት ባወጣው መግለጫ፣ “በአገሪቱ ሉዓላዊነት፣ ፀጥታ እና ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ወንጀሎችን ለማስቆም እርምጃ መውሰድ መጀመሩን” ገልጾ ነበር።
ነገር ግን ግለሰቦቹ እስከዛሬ ለፍርድ ሳይቀርቡ፣ ዝርዝር ክሳቸው በይፋ ሳይነገር እና መልስ የመስጠት መብት ሳያገኙ ቆይተው ደብዛቸው ከጠፋ ሩብ ክፍለ ዘመን ሆናቸው።
አምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጨምሮ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድርጅቶች ያለመደበኛ ክስ እና የችሎት ሂደት ለአስርት አመታት የተፈጸመውን እስር በተደጋጋሚ ያወገዙ ሲሆን፣ ታሳሪዎቹ “የህሊና እስረኞች” መሆናቸውን ይገልጻሉ።
ከ25 ዓመታት በኋላ አሁንም መልስ ያላገኘው ዋነኛው ጥያቄ ግን “እነዚህ ሰዎች የት ናቸው? ምን ደረሰባቸው? እና ለምን ወደ ፍርድ ቤት አልቀረቡም?” የሚለው ነው።
ቢቢሲ እነዚህ ባለሥልጣናት የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ ከኤርትራ መንግሥት መረጃ ለማኘት ጥያቄ አቅርቦ ምላሽ እየጠበቀ መሆኑን ዘግቧል።
ባለስልጣናቱ ጥያቄያቸው ምን ነበር? በመስከረም 1994 ዓ.ም የተሠራጨው የ15ቱ ቡድን አባላት ግልጽ ደብዳቤ ዋና ዋና ጥያቄዎች ኤርትራ በሰላማዊ፣ ሕጋዊ እና ዲሞክራሲያዊ መንገድ ከፖለቲካዊ ቀውሱ እንድትወጣ ጥሪ የሚያቀርብ እንደነበር ያሳያል።
ደብዳቤው ሰላማዊ እና ዴሞክራሲያዊ ውይይት እንዲካሄድ፣ የሕግ የበላይነት እና ፍትህ በአገሪቱ እንዲሰፍን እንዲሁም የተሳሰተውን አቅጣጫ ማረምን እና መፍትሄ ለማግኘት ያለመ ነበር።
ከነፃነት በኋላ ሥልጣን ቀስ በቀስ በጥቂቶች እጅ ውስጥ እየገባ መምጣቱ፣ የጋራ ውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ቅረቱ፣ ተጠያቂነት እና ተቋማዊ አሠራር እየተዳከሙ መምጣቱን የሚያትተው ደብዳቤ “አገሪቱ በሕገ መንግሥት፣ በሕግ፣ በተቋማት እና በሕዝብ ተሳትፎ መመራት” እንዳለባት ጠይቀው ነበር።
በተጨማሪም የተረቀቀው የኤርትራ ሕገ መንግሥት ተግባራዊ መሆን እንዳለበት እና የመንግሥት ሥልጣን በተለያዩ የሕግ ተቋማት መገደብ እና ቁጥጥር ሊኖርበት እንደሚገባ ይጠይቃል።
በተለይም ወሳኝ አገራዊ ጉዳዮች በአንድ ሰው ወይም በጥቂት ሰዎች ሳይሆን በጋራ ምክክር እና በሕግ ተቋማት እንዲወሰኑ፣ ገለልተኛ የምርጫ ኮሚሽን እንዲመሰረት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሕግ እንዲጸድቅ እና ምርጫ እንዲካሄድ የሚሉ ቁልፍ ጥያቄዎችም ይገኙበታል።
እንዲሁም በፕሬዝዳንቱ የተቋቋመው ልዩ ፍርድ ቤት እና ልዩ የምርመራ ኮሚቴ እንዲፈርስ፡ የዳኝነት አካላት ከአስፈፃሚው አካል ነጻ እንዲሆኑ፣ የፕሬስ፣ የመናገር እና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ዋስትና እንዲያገኝ ጠይቀው ነበር።
በቡድን 15 አባላት በተሠራጨው ግልጽ ደብዳቤ ለቀረቡት ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል የተባለው ተረቅቆ ወደ ተግባር ያልተቀየረው የኤርትራ ሕገ መንግሥት የጥያቄዎቹ ማዕከላዊ ነጥብ ነው። በዚህም አስካሁን በኤርትራ ተቃዋሚ ፓርቲ እና ነጻ መገናኛ ብዙኃን ካለመኖራቸው በተጨማሪ ኤርትራ ነጻ አገር ከሆነች ጊዜ አንስቶ ምርጫ አድርጋ አታውቅም።














